top of page

በወላጆቻቸው መታሰር ምክንያት ወደ ማረሚያ ቤት መግባት ግድ የሚሆንባቸው ህፃናት እንዴት ይሆን የሚስተናገዱት?

  • sheger1021fm
  • 3 hours ago
  • 2 min read

ህዳር 11 2018


ያለ ጥፋታቸው፤ በወላጆቻቸው መታሰር ምክንያት ወደ ማረሚያ ቤት መግባት ግድ የሚሆንባቸው ህፃናት በዚያ ሲገኙ እንዴት ይሆን የሚስተናገዱት?


እነርሱን ማዕከል ያደረገ አገልግሎትስ ያገኙ ይሆን? ስንል ጠይቀናል፡፡ ስለ ጉዳዩ የጠየቅነው ማረሚያ ቤቶችን የሚያስተዳድረው የፌድራሉ ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ምን አለ?


የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚው አቶ ገረመው አያሌው፤ እስካሁን የእነዚህን ህፃናት መብትና ጥቅም የሚያጠብቅ የህግ ማዕቀፍ የለም ብለውናል፡፡


ወደ ማረሚያ ቤቶች የሚገቡ ልጆች ከእናቶቻቸው ጋር ነው የሚገቡት፤ እስካሁን ባለው አሰራር ለህፃናቱ ተብሎ የሚመደብ በጀት ስለሌለ ህፃናቱ የእናቶቻቸውን ምግብ ተካፍለው ነው የሚመገቡት ያሉን የህግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ ህፃናቱ ከቀለብ ጀምሮ ሌሎችንም ማግኘት የነበረባቸውን ጥቅም እንዳያገኙ ሆኗል ብለዋል፡፡


ይህንንም በመረዳት የእነርሱን ጥቅም ሊያስጠብቅ የሚችል የህግ ማዕቀፍ እየተሰናዳ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ree

በማረሚያ ቤት ላሉ ህፃናት እስካሁን የህግ ማዕቀፍ ባይኖረውም ማረሚያ ቤቶቹ ለእናቶችና ለህጻናቱ ከምግብ ጀምሮ፣ የህፃናት ማቆያ በማዘጋጀት የተሟላ ለማድረግ ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ በትምህርት በኩልም ከመዋዕለ ህጻናት ጀምሮ መደበኛ ትምህርት እንደሚሰጥም ጠቅሰዋል፡፡


በማረሚያ ቤቶች ላሉ ህፃናት የሚመደብ በጀት ባለመኖሩ የሚያስፈልግቸውን አገልግሎት የሚሟላው ከለጋሽ ድርጅቶች የሚገኝን ድጋፍ በመጠበቅ ነው፤ የህግ ማዕቀፉ ተጠናቅቆ ወደስራ ሲገባ እነዚህን ችግሮች ይቀርፋል ብለን እንጠብቃለን ብለዋል፡፡


ያለ ጥፋታቸው የሚቀጡት እነዚህ ህፃናት ለተደራራቢ የስነ ልቦና ጫና ይጋለጣሉ፤ በዚህ በኩል የሚገጥማቸውን ችግር ለመቅረፍ ወደ ማረሚያ ቤት ሲገቡ ሊገጥማቸው ስለሚችለው ነገር እየነገሩ እራሳቸውን ከሁኔታው ጋር እንዴት ማስማማት እንዳለባቸው ምክር የሚሰጡ የስለ ልቦና ባለሙያዎች እንዳሉም ከአቶ ገረመው ሰምተናል፡፡


በጉዳዩ ላይ ሙያዊ ማብራሪያ የሰጡን የህግ ባለሙያና ጠበቃውአቶ ጥጋቡ ደሳለኝ ምን አሉ?


ኢትዮጵያ ተቀብላ የህጓ አካል ያደረገቻቸው አለም አቀፍ የህፃናት መብቶች ስምምነቶች ህፃናት በምንም ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑ ግልጽ የሆነ አያያዝና እንክብካቤ ሊያገኙ እንደሚገባ ያስቀምጣሉ ብለዋል፡፡


እንደሃገር ግልፅ የሆነ የማረሚያ ቤቶች ህፃናትን የተመለከተ የህግ ድንጋጌ ባይኖርም እነዚህን አለም አቀፍ መርሆች መከተል እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡


በኢትዮጵያ ያሉ ማረሚያ ቤቶች አይደለም ለህፃናቱ ለወላጆቻቸውም ምቹ እንዳልሆነ ይታወቃል የሚሉት የህግ ባለሙያው፤ እየተሰናዳ ነው በተባለው የህግ ማዕቀፍ መካተት አለባቸው ያሉትን ዘርዝረዋል፡፡


ለህፃናቱ ጥቅም ሲባል ከወላጆቻቸው መነጠል የለባቸውም፤ በመሆኑም በህግ ማዕቀፉ ለህፃናቱ በጀት፣ እንደየእድሜያቸው የትምህርትና የመጫወቻ ስፍራዎችና ሌላውም እንዲሟላላቸው የሚያግዝ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡


ምንታምር ፀጋው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

👇👇👇


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page