top of page

ለኢትዮጵያ ሁለተኛ የሆነው የዓይን ባንክ በጅማ ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ተነገረ፡፡

  • sheger1021fm
  • 13 hours ago
  • 2 min read

ህዳር 11 2018

 

ለኢትዮጵያ ሁለተኛ የሆነው የዓይን ባንክ በጅማ ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ተነገረ፡፡

 

የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ እንደተናገረው በአዲስ አበባ ዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል ውስጥ ካለው የአይን ባንክ በተጨማሪ ለረጅም ጊዜ ተይዞ በነበረ ዕቅድ በክልል ከተማ የዓይን ብሌን የሚሰበሰብበት ባንክ ተከፍቷል ብሏል፡፡

 

የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ሀብታሙ ታዬ እንደነገሩን ጅማ ላይ ተጨማሪ የዓይን ባንክ ለመክፈት የተጀመሩት ስራዎች ተጠናቀው ባንኩ ስራ እንዲጀምር ተደርጓል ብለዋል፡፡

 

በሀገሪቱ በአይን ብሌን ጠባሳ ምክንያት ከበጎ ፈቃደኛ ለጋሾች ድጋፍ የሚፈልጉ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን የሚናገሩት አቶ ሀብታሙ ካለው ፍላጎት አንጻር ሁለት የአይን ባንክ አሁንም በቂ አይደለም ይላሉ፤ የፍላጎት እና የአቅርቦት ልዩነቱ አሁንም ሰፊ ነው በሀገሪቱ ግማሽ ሚሊየን ያህል ሰዎች በአይን ብሌን ጠባሳ  ምክንያት ብርሃናቸውን እንዳጡ ይገመታል አሁን ያለን አዲስ አበባ ላይ ያለው ባንክ እና አሁን ጅማ ላይ የተከፈተው ብቻ ይሄንን ምላሽ መስጠት አይችልም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

 

ቀዶ ህክምናው በሚከናወንባቸው ሌሎች ክልሎች ላይ ከአዲስ አበባ ባንክ የተሰበሰበው ብሌን ነው የሚላከው እዛው ተመሳሳይ የብሌን መሰብሰቢያ ባንኮች መከፈት አለባቸው ብለዋል፡፡

 

አገልግሎቱን ከሚጠባበቁ ሰዎች አኳያ ታሳቢ በማድረግም ተጨማሪ የአይን ባንኮችን በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ለመክፈት የተያዘ እቅድ አለ ወይ ያልናቸው አቶ ሀብታሙ ስራው ብዙ መስፈርቶችን የሚጠይቅ ነው እንደ ላብራቶሪ ያሉ ተጨማሪ አገልግሎቶች ስለሚጠይቅ ያንን በአጭር ጊዜ ማሟላት አይቻልም ለጊዜው የተያዘ ዕቅድ ባይኖርም በረዥም ጊዜ ለመክፈት ጥናት የማጥናት ስራ ተጀምሯል በሀገሪቱ ከሚጠበቀው ቁጥር አኳያ ግን ሁለት ባንኮች በቂ አለመሆኑ ይታመናል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

 

በዓይን ብሌን ጠባሳ ምክንያት ብርሃናቸውን ላጡ ከእልፈት በኋላ ልገሳ ለማድረግ ቃል የሚገቡ ሰዎች በ2017 ዓ.ም የተሻለ ቁጥር ማሳየቱ ተነግሯል፡፡

 

በዛው ዓመት ከበጎ ፈቃደኞች ከተገኘ ልገሳ 150 ያህል ሰዎች ዳግም ማየት ችለዋል ተብሏል፡፡

 

የበጎ ፈቃደኛ ለጋሾችን ቁጥር አሁንም ለመጨመርም በተለያዩ መንገዶች የማሳወቅ ስራ እየከወነ መሆኑን ከኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ ሰምተናል፡፡

 

ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ….

 

ምህረት ስዩም

 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

👇👇👇

 

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page