top of page

ታሪክን የኋሊት -የማይጨው ጦርነት

  • 2 days ago
  • 2 min read

በኢትዮጵያና በኢጣሊያ መካከል የማይጨው ጦርነት የተደረገው በ1928 ዓ.ም በዛሬው ቀን ነበር፡፡


ኢጣሊያ በሊቢያና በሱማሊያ ከኢትዮጵያ ክፍል ኤርትራን በቅኝ ግዛትነት ይዛ ከቆየች በኋላ፣ ጠቅላላ ኢትዮጵያን በሃይል ለመውረር ጦርነት ከፈተች፡፡


በምፅዋ ወደብ ፣ በኤርትራ በኩል ወደወሰን ዘመናዊ የጦር ሃይሏን አደራጀች፡፡


የወልወልን ግጭት ሆን ብላ ከቀሰቀሰች በኋላ፣ ተበዳይ ሆና ለመቅረብ ሞከረች፡፡


አከታትላም ዋናው የጦር ሃይሏን ባደራጀችባት ኤርትራ በኩል፣ ወሰን ጥሳ፣ በጥቅምት ወር መቀሌን ያዘች፡፡


ከወራሪው የኢጣሊያ ሃይል ጋር ሲወዳዳር፣ ኋላ ቀርና አነስተኛ መሣሪያ ያለው አብዛኛው፣ የኢትዮጵያ ሰራዊት፣ የክተት አዋጁን ተከትሎ፣ ስንቁን ይዞ፣ ጦርና ጋሻውን አንግቦ ወደዘመቻው ተሰማራ፡፡


ኢጣሊያ፣ በሶማሊያ በኩል ባደራጀችው ዘመናዊ የጦር ሃይል፣ በምሥራቅ በዑጋዴንና በደቡብ በዶሎ በኩል፣ ጦርነት ጀመረች፡፡


ኢትዮጵያም ባላት ሃይል ለመከላከል ሰራዊቷን ወደ ሁለቱም የጦር ግንባር በእግር አጓጓዘች፡፡



#ማይጨው_ጦርነት በፊት፣ በርካታ ውጊያዎች ተደርገው ሰራዊትና አዛዞች ሞተዋል፡፡


የጎጃምና የጎንደር ጦር፣ በምዕራብ ትግራይ ተዋግቶ፣ እያሸነፈም፣ እየተሸነፈም በመጨረሻ በአይሮፕላን መርዝ ተጠቅቶ ተበትኗል፡፡


በጦር ሚኒስትሩ የሚመራው ከ50 ሺህ በላይ ይሆናል ተብሎ የተገመተው ጦርና ከወለጋ የተንቀሣቀሰው ጦር፣ በአምባአራዳምና በሌሎች ቦታዎች ተዋግቶ በአውሮፕላን መርዝና በኢጣሊያ ዘመናዊና ከባድ መሣሪያ ጉዳት ስለደረሰበት አዛዦችም ጭምር በጦር ሜዳ ተሰው፡፡


በተምቤን በኩል የዘመተው የሰላሌ፣ የደቡብ ጎንደር፣ የከምባታና የላስታ ጦርም ከታዘዘበት ቦታ ሳይደርስ ኢጣሊያኖች እየቆረጡ አጠቁት፡፡


በመጨረሻ ለሰባት ወራት፣ ኢትዮጵያኖች ሲፋለሙ ቆይተው፣ ከሞት የተረፉት አዛዦችና ወታደሮች ንጉሠ ነገሥቱ በሚመሩት ጦርነት ለመዋጋት ማይጨው ላይ ተሰበሰቡ፡፡


ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር አብሮ የዘመተው ተዋጊ፣ ከኢጣሊያኖች ጋር ሲወዳደር በቁጥርም፣ በመሣሪያ ጥራትም በብዙ ያንሳል፡፡


ያም ሆኖ የመጨረሻውን ውጊያ ለማድረግ በማይጨው ተሰለፈ፡፡


መጋቢት 22 1928 በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሚመራው የኢትዮጵያ ጦር በ3 ግንባር ተሰለፈ፡፡


በጄኔራል ባዶሊዩ የሚመራው የኢጣሊያ ሰራዊትም በዘመናዊ መድፎችና ከ70 በላይ በሚደርሱ የጦር አይሮፕላንኖች እየታገዘ ተሰለፈ፡፡


ከንጋቱ 11፡00 ጦርነቱ ተጀመረ፡፡


ውጊያው እንደተጀመረ ኢትዮጵያኖች ኢጣሊያኖች ካምፕ ድረስ ዘልቀው በሚያስደንቅ ጀግንነት ተዋጉ፡፡


ባዶሊዩ ገና በጠዋቱ፣ የጦር አይሮፕላኖቹ በሙሉ ሃይላቸው በቦምብና በመርዝ ጋዝ ኢትየጵያኖቹን እንዲደበድቡ አዘዘ፡፡


ከፍተኛ እልቂት ሆነ፡፡ ምንም መከላከያ የሌላቸው ኢትዮጵያኖች ከውጊያ ውጭ ሆኑ፡፡


የኢትዮጵያ ሠራዊት ምሽት ድረስ ከተዋጋ በኋላ ወደኋላው አፈገፈገ፡፡


ጣሊያኖችም የሚሸሸውን ሠራዊት እየተከታተሉ የመርዝ ጋዝ እየረጩ ፈጁት፡፡


የማይጨው ጦርነት፣ በዚያኑ ዕለት በኢጣሊያኖች ድል አድራጊነት ተጠናቀቀ፡፡


የማይጨው ጦርነት ከተደረገ 90 ዓመት ሆነ፡፡


እሸቴ አሰፋ


መጋቢት 22/2018


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


YouTube : https://shorturl.at/18TS1

WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx

X :- https://x.com/shegerfm?s=2

Recent Posts

See All
የኤሌክትሪክ ኬብሎችን የዘረፉ ግለሰቦች በህግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተናገረ።

መጋቢት 23/2018 የኤሌክትሪክ ኬብሎችን የዘረፉ ግለሰቦች በህግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተናገረ። ከ3.8 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኤሌክትሪክ ኬብሎችን የዘረፉ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አገልግሎቱ ተናግሯል። የየካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የደረሰው

 
 
 

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page