top of page

ታህሳስ 8፣2016 - የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በብዙ አስቸጋሪ ሁኔታ ዉስጥ ናቸው ተባለ

የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በብዙ አስቸጋሪ ሁኔታ ዉስጥ ናቸው ተባለ፡፡


ካሉበት አስቸጋሪ ሁኔታ ለመውጣትም የሚመሩበት ስርዓታቸውንና ፖሊሲዎቻቸውን በጥልቀት ሊፈትሹ እንደሚገባም ተነግሯል፡፡


በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በትምሀርት ሚኒስቴርና በትምህትና ስልጠና ባለስልጣን አማካኝነት እየተላለፉ ያሉት መምሪያዎች ከቀድሞው በበዙ የተለዩ በመሆናቸው የግል የትምህት ተቋማቱም ከጊዜውና ከሚወጡ መመሪያዎች እራሳቸውን ማስማማት የግድ ይላቸዋል ተብሏል፡፡


የግል የትምህርት ተቋማት የሚመሩበት ስርዓትና አካሄዳቸውን የማያሻሽሉ ከሆነና አሁን በያዙት መንገድ እነቀጥላለን የሚሉ ከሆነ የህልውናቸው ጉዳይም አደጋ ውስጥ እንደሚገባም ተነግሯል፡፡


ይህ የተነገረው የኢትዮጵያ የግል የከፍተኛ ትምህርት እና የቴክኒክና ሞያ ስልጠና ተቋማት ማህበር የ2016 ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን ባደረገበት ወቅት ነው፡፡


በመድረኩ የማህበሩ ፕሬዝደንት አረጋ ይርዳው (ዶ/ር) የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የገጠሟቸውን ችግሮችና ፈተናዎች አብራርተዋል፡፡


ለዘርፉ እንደ ዋነኛ ችግር ናችው ተብለው ከተነሱት መካከል በተቋማቱ ለመማር የሚመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር እጅግ መቀነሱ አንደኛው ነው ተብሏል፡፡


ይህም የ12ተኛ ክፍል ፈተናን የማለፊያ ነጥብ የሚያመጡ ተማሪዎች ቁጥር እጅግ ከመቀነሱ ጋር የተያያዘ እንደሆነም ዶ/ር አረጋ ጠቅሰዋል፡፡


በተጨማሪም በዚህ ዓመት የተጀመረው የሁለተኛ ዲግሪን ለመማር እንደ ቅድመ መስፈርት የተደረገውን የመግቢያ ፈተናን ያለፉ ተማሪዎች ቁጥር ዝቅተኛ መሆን ሌላኛው ምክንያት እንደሆነም ፕሬዝደንቱ አውርተዋል፡፡


ለዘርፉ በሀላፊነት እንዲያገለግሉ የሚመደቡ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ባጠረ ጊዜ፣ በተደጋጋሚ የሚቀያየሩ መሆኑ ዘርፉን ሳያወቁትና ሳይረዱት የተለያየ አሰራር ተግባራዊ ማድረጋቸውም የግል የግል የከፍተኛ ት/ት ተቋማት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው ሲሉ ዶ/ር አረጋ ይርዳው ጠቅሰዋል፡፡


በትምህርት ሚኒስቴር የአካዳሚ ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ኤባ ሚጀና በበኩላቸው በትምህርት ሚኒስቴር የሚወሰዱ እርምጃዎችና መመሪያዎች ለትምህርት ጥራት መሻሻል ሲባል ነው ብለዋል፡፡


በኢትዮጵያ የትምህርት ተደራሽነት በአንፃራዊነት የተሻለ ቢሆንም በጥራቱ ጉዳይ ግን አሁንም መስራት ይገባል ሲሉ ዶ/ር ኤባ ሚጀና በመድረኩ ተናግረዋል፡፡

የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመሩበትን ስርዓትና ፖሊሲዎቻቸውን ከማሻሻል ባለፈ ወደ ቴክኒክና ሞያ ትምህርት ትኩረት እንዲያደርጉ እንዲሁም 20ም ወይም 30ም ሆነው በአንድ ላይ እንዲጣመሩ ማድረግ ከተጋፈጡት ችግር ለመውጣት እንደመፍትሄ ተለይተው የቀረቡ ሃሳቦች እንደሆኑ በመድረኩ ሲነገር ሰምተናል፡፡


በአሁን ወቀት በኢትዮጵያ 366 የግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ ሲሆን ዛሬ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን ያደረገው ‘’የኢትዮጵያ የግል የከፍተኛ ትምህርት እና የቴክኒክና ሞያ ስልጠና ተቋማት ማህበር’’ ደግሞ 176ቱን በአባልነት ያቀፈ ነው፡፡



ማንያዘዋል ጌታሁን



የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz



bottom of page