top of page

ታህሳስ 16፣2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • Dec 25, 2024
  • 2 min read

 

ንብረትነቱ የአዘርባጃን አየር መንገድ የሆነ የመንገደኞች ማጓጓዣ አውሮፕላን በካዛክስታን ተከሰከሰ፡፡

 

አውሮፕላኑ የተከሰከሰው ከ60 በላይ መንገደኞችን እንዳሳፈረ መሆኑን ሒንዱስታን ታይምስ ፅፏል፡፡

 

ከ14 ያላነሱ ሰዎች ከአደጋው በሕይወት መትረፋቸው ተነግሯል፡፡

 

አደጋ የገጠመው አውሮፕላን ቀደም ሲል በሩሲያ ቼችኒያ ግሮዝኒ እንዲያርፍ የታቀደ ነበር ተብሏል፡፡

 

ሆኖም በግሮዝኒ ከባድ ጭጋጋማ የአየር ሁኔታ ስለገጠመው የበረራ መስመሩን ለመቀየር መገደዱ ተሰምቷል፡፡

 

አውሮፕላኑ በጭጋግ ምክንያት አቅጣጫውን ከቀየረ በኋላ በካዛክስታኗ አክታው ከተማ አቅራቢያ መከስከሱ ታውቋል፡፡

 

በሕይወት ተራፊዎቹ ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸው ተሰምቷል፡፡

 

በሱዳን የረሃቡ አድማስ እየሰፋ ነው ተባለ፡፡

 

በአገሪቱ 5 የተለያዩ ስፍራዎች የረሃቡ አድማስ እየሰፋ መሆኑን እወቁልኝ ያለው IPC የተሰኘው አለም አቀፍ ተቋም እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡

 

እንደ ተቋሙ መረጃ በአሁኑ ወቅት 24 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሱዳናውያን አጣዳፊ የምግብ እርዳታ ያሻቸዋል፡፡

 

የአገሪቱ መንግስት ጦር እና በምህፃሩ RSF የተሰኘው ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ጦርነት ማካሄድ ከጀመሩ ከአመት ከ8 ወራት በላይ ሆኗቸዋል፡፡

 

ጦርነቱ ዓይነተ ብዙ እየሆነ የመጣውን ሰብአዊ ቀውስ እያከፋው ነው፡፡

 

በሱዳን የጦርነቱ መቆሚያ ምልክት አይታይም፡፡

 

 

በሶሪያ የቀድሞውን አስተዳደር ያባረሩት አማጺ ቡድኖች በአንድ የመከላከያ ሚኒስቴር እዝ ስር ለመጠቃለል ተስማሙ ተባለ፡፡

 

ስምምነቱን የአዲሱ ጊዜያዊ አስተዳደር መሪ አህመድ አል ሻራ ማብሰራቸውን አልጀዚራ ፅፏል፡፡

 

ስምምነት የተደረሰው በአልሻራ እና በታጣቂ ቡድኖቹ መሪዎች መካከል በተደረገ ንግግር መሆኑ ታውቋል፡፡

 

ይሁንና በአገሪቱ ሰሜናዊ ምስራቅ ያለው እና በምህፃሩ SDF የተሰኘው የኩርዶች ታጣቂ ቡድን የዚህ ስምምነት አካል አይደለም ተብሏል፡፡

 

SDF በቀጠናው የአሜሪካውያን አጋር ሆኖ መቆየቱ ይነገራል፡፡

 

ቱርክ ደግሞ SDFን በአሸባሪነት የፈረጀችው የኩርዲስታን ሰራተኞች ፓርቲ PKK አንድ አካል አንድ አምሳል አድርጋ እንደምትቆጥረው መረጃው አስታውሷል፡፡

 

 

በሩሲያ ስለላ ሲፈፅም ተገኝቷል የተባለ አሜሪካዊ የ15 አመታት የእስር ቅጣት ተፈረደበት፡፡

 

ኢውጌኒ ስፔክተር የተባለው አሜሪካዊ በስለላ ተጠርጥሮ ከተያዘ በኋላ 3 አመት ከመንፈቅ በእስር ማሳለፉን አረብ ኒውስ ፅፏል፡፡

 

በሩሲያ ቢወለድም ዜግነቱ አሜሪካዊ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

 

ከመያዙ አስቀድሞ በሩሲያ የአንድ የካንሰር መከላከያ መድሐኒት አቅራቢ ኩባንያ የቦርድ ሊቀ መንበር ነበር ተብሏል፡፡

 

የስለላ ወንጀሉ ምንነት ግን በዝርዝር አልተጠቀሰም፡፡

 

ለአንድ ሩሲያዊ የቀድሞ ከፍተኛ ሹም ጉቦ በመስጠቱ ረገድ አግዟል መባሉ ጥፋተኛ ከተባለባቸው ጉዳዮች አንዱ ነው ተብሏል፡፡

 

የኔነህ ከበደ

 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

 

📌 YouTube: https://t.ly/9uH-g

 

 

 

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page