top of page

ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ፣ በፋሽስት ጣሊያን ሰማዕትነት የተቀበሉት በ1928 ዓ.ም በዛሬው ቀን ነበር፡፡

  • 1 hour ago
  • 2 min read

ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ፣ በፋሽስት ጣሊያን ሰማዕትነት የተቀበሉት በ1928 ዓ.ም በዛሬው ቀን ነበር፡፡




ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ፣ መስቀልና ወንጌል ብቻ ይዘው የወራሪውን የኢጣሊያ ፋሽስት ፣ ነውሩንና ግፉን ፊት ለፊት ታግለው፣ ለሃገራቸውና ለሃይማኖታቸው ሕይወታቸውን አሳልፈው የሰጡ ፣ በጳጳስ ናቸው፡፡


አባ ኃይለማርያም፣ ከመጀመሪያዎቹ አራት ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት አንዱ ሆነው ሲመረጡ ስማቸው ብፅዕ አቡነ ጴጥሮስ ሆነ፡፡


በቅኔ ፣ በዜማ ፣ በመፃህፍት ትርጓሜ የተመረቁት አቡነ ጴጥሮስ፣ በ1921 ዓ.ም ጳጳስነት ከተሾሙ በኋላ፣ የኢጣሊያ ወረራ እስከገፋበት ድረስ ወሎንና ከሸዋ መንዝን እና ኤፍራታን፣ ግሺንና አንጾኪያን ሃገረ ስብከታቸው አድርገው ቆይተዋል፡፡


ከዚያ በፊትም በወላይታና በዝዋይ በመምህርነት አገልግለዋል፡፡


በማይጨው ዘመቻ ጊዜ ፣ ከንጉሰ ነገስቱ ጋር ሳይለዩ በማይጨው ተዋጊውን ሰራዊት እያበረታቱ አዋግተዋል፡፡


ኢትዮጵያዊያኑ ድል ሆነው ሲያፈገፈጉ በትውልድ አካባቢያቸው በሰላሌ ከተሰማሩት አርበኞች ከነዳጃዝማች አበራ ካሣ ጋር ተቀላቅለው ቆዩ፡፡


በ1928 ሐምሌ ወር አዲስ አበባን ከኢጣሊያኖች ለማስለቀቅ በተደረገው ከበባ በሰሜን በኩል ከዘመቱት አርበኞች ጋር አዲስ አበባ ደረሱ፡፡


አርበኞች አልቀናቸውም፡፡ ድል ሆነው ሲመለሱ ብፅዕ አቡነ ጴጥሮስ ግን ለመመለስ አልፈለጉም፡፡


ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን ፀሎት አድርገው በቀጥታ ወደመሐል ከተማ ገብተው ተያዙ፡፡


የኢጣሊያ ሹማምንት ፣ አቡነ ጴጥሮስን አባበሉዋቸው፡፡


የኢጣሊያን ገዥነት ካመኑ በክብር እንደሚያዙ ነገሩዋቸው፡፡


ጳጳሱ ግን እምቢ አሉ፡፡ ገንዘብህ ለጥፋትህ ይሁን ብለው ረገሙ፡፡ እንኳንስ ሰው፣ ምድሩዋ እንዳትገዛ አወገዙ፡፡


በአቡነ ጴጥሮስ ድርጊት የተናደደው ጀኔራል ግራዚያኒ ፣ እንዲገደሉ ወሰነባቸው፡፡


ሐምሌ 22-1928 ዓ.ም ፣ ብፅዕ አቡነ ጴጥሮስ ፣ በሰንሰለት ታስረው ፣ ከአራዳ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በስተምዕራብ ባለው ቦታ ቆሙ፡፡


ከኋላቸው 8 ወታደሮች ጠመንጃቸውን ወድረው ተሰልፈዋል፡፡ በጊዜው በቦታው የነበረው ጋዜጠኛ እንደፃፈው ጥቁሩ ቀሚሳቸው ጭቃ ነክቶታል፡፡


ወንጌላቸውንና መስቀላቸውን ይዘዋል፡፡ ግድያቸውን እንዲመለከት በትዕዛዝ የተሰበሰበው ሕዝቡም ሆነ ምድሩዋ እንዳትገዛላት አወገዙ፡፡


ከረፋዱ 5፡30 ሆኖ ነበር፡- ይልና ጋዜጠኛው ስላሟሟታቸው እንዲህ ይላል፡፡ “አንድ መኮንን ውሳኔውን እየተንቀጠቀጠ ሲያነብ ፣ እሳቸው ግን ያለምንም ስጋት ያዳምጡት ነበር፡፡


“ወዲያው ዓይንዎ እንዲሸፈን ይፈልጋሉ?” ሲል ጠየቃቸው፡፡ “እሱ የናንተ ተግባር ነው” አሉት፡፡


ትዕዛዝ ሲሰጣቸው ወታደሮቹ ተኮሱ፡፡


በስምንት ጥይትም መቷቸው፡፡ ግን አልሞቱም ነበርና ፣ ኮሎኔሉ በሶስት የሽጉጥ ጥይት፣ ራስ ቅላቸው ላይ ተኩሶ ገደላቸው፡፡


ሕዝቡም በሀዘን ተመታ” ይላል፡፡ ጋዜጠኛው ፣ ንብረታቸውን ወስደሁ ያለው ወታደር እንደነገረው ፣ ወንጌላቸውና መስቀላቸው በጥይት ተበሳስቷል፡፡


አቡነ ጴጥሮስ በ53 ፣ አመታቸው ፣አሁን ሐውልታቸው በቆመበት አካባቢ ተገድለው ባልታወቀ ቦታ ተቀብረዋል፡፡


ከነፃነት በኋላ በ1938 ለመታሰቢያ እንዲሆን ሐውልት ተቀርፆ ቆመላቸው፡፡


አሁን ያለው ሐውልት ለሁለተኛ ጊዜ ተሻሽሎ ተቀርፆ የቆመላቸው ነው፡፡ በፍቼም ለሶስተኛ ጊዜ ሐውልት ተቀርፆላቸዋል፡፡


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በሙሉ ድምፅ በወሰነው መሰረት ፣ ሰማዕትነታቸውን አፅድቆ በስማቸው ቤተ ክርስቲያን ተሰርቶላቸዋል፡፡


ሰማዕተ ፅድቅ አቡነ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን ፣ የታነፀው በትውልድ ቀያቸው በፍቼ ነው፡፡


የብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕትነት የብዙ የጥበብ ሰዎችን ስሜት እየገዛ ገጣሚዎች ገጥመውላቸዋል፣ ቅኔ አዋቂዎች ቅኔ ዘርፈውላቸዋል ፣ ድራማ ተሰርቶላቸዋል፡፡


ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በፋሽስቶች ከተገደሉ 90 አመት ሆነ፡፡



እሸቴ አሰፋ

Recent Posts

See All
አስተማማኝ የጤና ሥርዓት ለመገንባት በሀገር ውስጥ የመድኃኒት ምርትን ማጠናከርና የፀረ-ተሕዋስያን መድኃኒቶችን አጠቃቀም ቁጥጥር ማጠናከር እንዲሁም የፋርማሲ ዘርፍ ጥናትና ምርምር ማሳደግ ያስፈልጋል ተባለ።

ሐምሌ 22 2018 አስተማማኝ የጤና ሥርዓት ለመገንባት በሀገር ውስጥ የመድኃኒት ምርትን ማጠናከርና የፀረ-ተሕዋስያን መድኃኒቶችን አጠቃቀም ቁጥጥር ማጠናከር እንዲሁም የፋርማሲ ዘርፍ ጥናትና ምርምር ማሳደግ ያስፈልጋል ተባለ። አስተማማኝ የጤና ሥርዓት ለመገንባት ኢትዮጵያ በመድኃኒት ምርት ራሷን መቻል እንዳለባት፣ በተ

 
 
 
ኢትዮጵያ የምታመነጨው የኤሌክትሪክ ሀይል መጠን 9 ሺህ 730 ሜጋ ዋት ደርሷል፡፡

ሐምሌ 22 2018 ኢትዮጵያ የምታመነጨው የኤሌክትሪክ ሀይል መጠን 9 ሺህ 730 ሜጋ ዋት ደርሷል፡፡ ከዚህ ውስጥ ከውሃ የሚመነጨው ድርሻው ከ95 እስከ 96 በመቶ ነው ተብሏል፡፡ ኢትዮጵያ ከውሃ በተጨማሪ እንደ ነፋስ ፣ ፀሀይ እንፋሎት ካሉና ሌሎች አማራጮች ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ሀይል በማመንጨት ስብጥሩን የማስፋት ው

 
 
 

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play
  • Facebook
  • X
  • Youtube
  • TikTok
  • Telegram
  • Whatsapp

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page