top of page

አስተማማኝ የጤና ሥርዓት ለመገንባት በሀገር ውስጥ የመድኃኒት ምርትን ማጠናከርና የፀረ-ተሕዋስያን መድኃኒቶችን አጠቃቀም ቁጥጥር ማጠናከር እንዲሁም የፋርማሲ ዘርፍ ጥናትና ምርምር ማሳደግ ያስፈልጋል ተባለ።

  • 2 hours ago
  • 2 min read

ሐምሌ 22 2018


አስተማማኝ የጤና ሥርዓት ለመገንባት በሀገር ውስጥ የመድኃኒት ምርትን ማጠናከርና የፀረ-ተሕዋስያን መድኃኒቶችን አጠቃቀም ቁጥጥር ማጠናከር እንዲሁም የፋርማሲ ዘርፍ ጥናትና ምርምር ማሳደግ ያስፈልጋል ተባለ።


አስተማማኝ የጤና ሥርዓት ለመገንባት ኢትዮጵያ በመድኃኒት ምርት ራሷን መቻል እንዳለባት፣ በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተባባሰ በመጣው የፀረ-ተሕዋስያን መድኃኒቶችን የመቋቋም ችግር ለመቀነስ የፋርማሲ ባለሙያዎችና የመድኃኒት ኢንዱስትሪው ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ተነግሯል።


ዓመታዊው የኢትዮጵያ ፋርማሲ ማህበር የሳይንስ ኮንፈረንስ እና ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬ በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና መስሪያ ቤት ተጀምሯል።


በዚህ ዓመት የተመረጠው የኮንፈረንሱ መሪ ቃል በዓለም አቀፍ የጤና ዘርፍ አንዱ ከፍተኛ ስጋት ተብሎ በሚታየው የፀረ-ተሕዋስያን መድኃኒቶችን የመቋቋም ችግር ላይ ነው።


ጉባኤው "የፋርማሲ ባለሙያዎችን በጤና አጠባበቅ ውስጥ እንደ ቁልፍ መሪዎች ማብቃት፤ ፀረ-ተሕዋስያን መድኃኒቶችን መቆጣጠር፣ ፈጠራን ማበረታታት እና ለወደፊቱ ዘላቂ የሆኑ የትብብር ልምዶችን ማሳደግ” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ነው።


የፋርማሲ ሙያውን ለማጠናከርና የመድኃኒት አቅርቦት ሥርዓቱን ለማሻሻል ማህበሩ ለረጅም ዓመታት አስተዋጽኦ ሲያበረክት መቆየቱን የኢትዮጵያ ፋርማሲ ማህበር ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዳንኤል ዋቅቶላ ተናግረዋል።


በዓለም ዙሪያ እየጨመረ የመጣውን የፀረ-ተሕዋስያን መድኃኒቶችን የመቋቋም ችግር ለመቀነስ፣ የመድኃኒት አመራረትና ጥራትን ለማረጋገጥ የፋርማሲ ዘርፉ ከጤናው ዘርፍ ጋር በመሆን ትልቅ ኃላፊነት ወስዶ እየሠራ እንደሚገኝም የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱልቃድር ገልገሎ ተናግረዋል።


በዘርፉ ያሉ የሎጂስቲክስና የመድኃኒት አቅርቦት ችግሮችን በመፍታት የመድኃኒት ተደራሽነትን ማሻሻል፣ የሀገር ውስጥ መድኃኒት ምርትን ማጠናከር እና ጥራት ያላቸውን መድኃኒቶች በቋሚነት ማቅረብ ቀዳሚ ትኩረት ከሚሰጣቸው ጉዳዮች መካከል ናቸውም ብለዋል።


የኢትዮጵያን የፋርማሲ ሥርዓት ለማጠናከር በዘርፉ የሚካሄዱ ጥናቶችና ምርምሮች የማይተኩ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ጠቅሰው፣ በማስረጃ ላይ የተመሠረቱ ውሳኔዎች ለጤና ሥርዓቱ መሻሻል መሠረት እንደሚሆኑ አስረድተዋል።


በመድኃኒት ምርትና አቅርቦት ዘርፍ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ተወዳዳሪና ተመራጭ ሀገር ለመሆን የባለሙያዎችን ሥነ-ምግባር ማጠናከር፣ በምርምርና በፈጠራ ላይ በስፋት መሥራት፣ እንዲሁም የመንግሥት፣ የግሉ ዘርፍና የአካዳሚያዊ ተቋማት ትብብር ሊጠናከር እንደሚገባም አሳስበዋል።


ዓመታዊ ኮንፈረንሱ በሀገሪቱ ውስጥ በፋርማሲና በጤና ዘርፍ ከሚካሄዱ ትልልቅ ሳይንሳዊ መድረኮች አንዱ በመሆን የምርምር ውጤቶችን፣ አዳዲስ ፈጠራዎችን እና ለፖሊሲ የሚጠቅሙ ምክረ ሐሳቦችን ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።


በኮንፈረንሱ የሚቀርቡ ሳይንሳዊ ጥናቶችና ውይይቶች የሚወጡባቸው ምክረ ሐሳቦች የፋርማሲ ሙያን ለማጠናከር፣ የመድኃኒት አጠቃቀምን ለማሻሻል፣ የምርምር ሥራዎችን ለማበረታታት እና በኢትዮጵያ የጤና ሥርዓት ውስጥ የፋርማሲ ባለሙያዎችን ሚና ለማሳደግ አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉ ተነግሯል።


46ኛው የኢትዮጵያ ፋርማሲዩቲካል ማህበር ዓመታዊ የሳይንስ ኮንፈረንስና የጥናት ጉባኤ እስከ ነገ ድረስ የሚቀጥል ሲሆን፣ በርካታ ሳይንሳዊ ጥናቶች፣ የፓናል ውይይቶች እና የሙያ ልምድ ልውውጦች ይካሄዱበታል ተብሏል።


በጉባኤው ላይ የፋርማሲ ባለሙያዎችን፣ የጤና ተቋማት አመራሮች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ የመንግሥት ተቋማት፣ የልማት አጋሮችንና የግሉ ዘርፍ ተወካዮች ተገኝተዋል።


የኢትዮጵያ ፋርማሲዩቲካል ማህበር በ1974 ዓ.ም. የተመሠረተና የፋርማሲ ሙያን ለማሳደግ፣ የሙያ ሥነ-ምግባርን ለማጠናከር፣ በማስረጃ ላይ የተመሠረቱ የጤና ፖሊሲዎችን ለመደገፍ እና ሕብረተሰቡ ጥራት ያለው የፋርማሲ አገልግሎት እንዲያገኝ እየሠራ እንደሚገኝ ሰምተናል።



ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ...




ምህረት ስዩም

Recent Posts

See All
ኢትዮጵያ የምታመነጨው የኤሌክትሪክ ሀይል መጠን 9 ሺህ 730 ሜጋ ዋት ደርሷል፡፡

ሐምሌ 22 2018 ኢትዮጵያ የምታመነጨው የኤሌክትሪክ ሀይል መጠን 9 ሺህ 730 ሜጋ ዋት ደርሷል፡፡ ከዚህ ውስጥ ከውሃ የሚመነጨው ድርሻው ከ95 እስከ 96 በመቶ ነው ተብሏል፡፡ ኢትዮጵያ ከውሃ በተጨማሪ እንደ ነፋስ ፣ ፀሀይ እንፋሎት ካሉና ሌሎች አማራጮች ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ሀይል በማመንጨት ስብጥሩን የማስፋት ው

 
 
 

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play
  • Facebook
  • X
  • Youtube
  • TikTok
  • Telegram
  • Whatsapp

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page