በፍትህ ሚኒስቴር የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ 1800 የሚሆኑ ሰዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ አዘዋውሯል ባላቸው 28 ተከሳሾች ላይ ክስ መመስረቱን ተናገረ፡፡
- sheger1021fm
- 2 days ago
- 2 min read
ጥር 19/2018
በፍትህ ሚኒስቴር የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ 1800 የሚሆኑ ሰዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ አዘዋውሯል ባላቸው 28 ተከሳሾች ላይ ክስ መመስረቱን ተናገረ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በህገ ወጥ መንገድ ሲያዘዋውሯቸው ከነበሩት ሰዎች ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰባቸውን ዐቃቤ ህግ በክሱ ጠቅሷል፡፡
የዐቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያስረዳው ክስ የመሰረተባቸው 28ቱ ግለሰቦች በሰው ልጅ ለመነገድ በማሰብ #የወንጀል_ቡድን በማደራጀት እንዲሁም የቡድኑ አመራር እና አባላት በመሆን በወንጀል ድርጊቱ ላይ ተሳተፈዋል በሚል የተጠረጠሩ ናቸው፡፡
በስራቸው ሌሎች አነስተኛ ስራ የሚሰሩ ደላሎችን በመመልመል ሰዎች በሊቢያ በኩል አድርገው ወደ አውሮፓ ከገቡ የተሻለ ኑሮ እንደሚኖሩ በማሳመን ወደ ባህርዳር እና ጎንደር ሲልኩ ቆይተዋል ብሏል፡፡
ተከሳሾቹ በባህር ዳር እና ጎንደር አካባቢ ሰዎችን ወደ ሱዳን ድንበር የሚያጓጉዙ ተቀጣሪዎችን በማዘጋጀት ኢ-መደበኛ በሆነ መንገድ ከሀገር ሲያስወጡ እንደቆዩም ጠቅሷል፡፡
ሰዎችን ከኢትዮጵያ ድንበር ካስወጡ በኋላ በዘረጉት የወንጀል መረብ አማካኝነት ወደ ሊቢያ ወስደው በመጋዘኖች ሲያጉሩ እንደነበርም አመልክቷል፡፡
በሊቢያ በሚገኙ ተከሳሾች እና ግብረ አበሮቻቸው በሚያስተዳድሩት መጋዘኖች ውስጥ በህይወት ለመቆየት ብቻ የሚበቃቸውን ምግብ እንዲያገኙ አድርገዉ ከያዙ በኋላ ወደ ቤተሰቦቻቸው ስልክ በመደወል ከፍተኛ ገንዘብ በመጠየቅ እስኪከፈል በእዳ መያዣነት ሲይዙ እንደቆዩም ጠቅሷል፡፡

በፍጥነት ገንዘብ ለመክፈል ላልቻሉ የተበዳይ ቤተሰቦች ተበዳዮችን እጅግ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ እየደበደቡ እና እያሰቃዩ በተንቀሳቃሽ ምስል በመቅረፅ ወደ ቤተሰቦቻቸው በመላክ ገንዘቡ እንዲከፈል ጫና ሲያሳድሩ ነበርም ብሏል፡፡
የተበዳይ ቤተሰቦች ገንዘብ አፈላልገው ለመክፈል ፍቃደኛ ሲሆኑ አሁን በሕግ ቁጥጥር ስር ውለው ክስ የቀረበባቸው ስምንት ተከሳሾች እና ሌሎች ግብረ አበሮቻቸውን የባንክ ሂሳብ በመጠቀም ገንዘብ ሲሰበስቡ እንደቆዩ የዐቃቤ ሕግ ክስ ያሳያል፡፡
በዚህም በሕግ ቁጥጥር ስር ሆነው ክስ በተመሰረተባቸው ስምንት ገንዘብ ሰብሳቢዎች አማካኝነት ብቻ ብር ሁለት ቢሊዮን አንድ መቶ ስልሳ ሚሊዮን ስምንት መቶ ስልሳ ሶስት ሺህ ሶስት መቶ ስልሳ አንድ ብር መሰብሰባቸውን ክሱ ያሳያል፡፡
ሌሎች ተከሳሾች በስምንቱ ተከሳሾች እና የተቀሩ ግብረ-አበሮቻቸዉ የሰበሰቡትን ገንዘብ በፍጠነት በመቀባበል በገንዘቡ ሲጠቀሙ እና ለግብረአበሮቻቸው ክፍያ ሲፈፅሙ ቆይተዋልም ብሏል፡፡
ከዝውውር ወጪ የተረፈ ቀሪ ገንዘብን ከሀገር እንዲሸሽ በማድረግ በውጪ ሀገር ሃብት አፍርተውበት እንዲሁም በሀገር ውስጥ ቋሚ እና ተንቀሳቃሽ ንብረቶች አፍርተውበት ተገኝተዋል ሲል የዐቃቤ ሕግ ክስ ዘርዝሯል።
በተከሳሾች በጠቅላላ አንድ ሺህ ስምንት መቶ ሰው በሕገ-ወጥ መንገድ ተዘዋውሯል ያለው ዐቃቤ ህግ በተደረገው ምርመራ የሰማንያ አምስት ሰዎች ማንነት የተለየ መለየቱን ከእነዚህ መካከል የሁለት ህይወት ማለፉ እንደተረጋገጠ ጠቅሷል።
በድብደባ ምክንያት ለበሽታ የተዳረጉ እና አስራ አምስት ሰዎች የደረሱበት ያልታወቀ መሆኑ ተረጋግጦ በክሱ ተካቷልም ብሏል፡፡
በከባድ የሰው ልጅ መነገድ ወንጀል፣ በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ፤ ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትና ሌሎች ወንጀሎች ክስ እንደተመሰረተባቸውም አመልክቷል።
ተከሳሾች ያፈሩት ቤቶች፣ ተሽከርካሪዎች እና ሰባ አንድ ሚሊዮን ሶስት ሺህ ሁለት መቶ አስራ አራት ብር ተለይቶ ለማካካሻነት ታግዶ እንደሚገኝም ጠቅሷል፡፡
ክሱ የቀረበው በሊቢያ መስመር በሰው ልጅ ከሚነግዱ ዋና ዋና አዘዋዋሪዎች ላይ ትኩረት አድርጎ በተካሄደ ምርመራ መነሻ እንደሆነ በበፍትህ ሚኒስቴር የማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይ የሰፈረው የዐቃቤ ህግ የወንጀል ክስ ዝርዝር ያሳያል።
በወንጀል ምርመራዉ ስራ የፍትሕ ሚኒስቴር፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ ዋና መምሪያ፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት፣ የፋይናንስ መረጃ ደህንነት እና ሌሎች ተቋማት መሳተፋቸውንም ጠቅሷል፡፡
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
YouTube : https://shorturl.at/18TS1
Telegram : https://shorturl.at/68aeK
Facebook፡ https://shorturl.at/tm5Q4
WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx
X :- https://x.com/shegerfm?s=2
LinkedIn: https://shorturl.at/Vfe6i
Tiktok : https://url-shortener.me/2DUB
Instagram: https://url-shortener.me/2DUD












Comments