በፌደራል መንግስትና በህወሓት መካከል የቀጠለው ውጥረት ወደ ዳግም አውዳሚ ጦርነት እንዳያመራ የሰላም ጥረቶች እንዲቀጥሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠይቀዋል
- sheger1021fm
- Nov 4
- 2 min read
ጥቅምት 25 2018
በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል የቀጠለው ውጥረት ወደ ዳግም አውዳሚ ጦርነት እንዳያመራ ሁሉም ዓይነት የሰላም ጥረቶች እንዲቀጥሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠይቀዋል፡፡
የሰሜን ዕዝ የተጠቃበትን 5ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በተሰናዳ ፕሮግራም ላይ ንግግር ያደረጉት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ህወሓት ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ ያደረጋቸው “ትንኮሳዎች፣ እምቢ ባይነቶች፣ ስራዎች እና ሴራዎች” ወደ ጦርነት ለመግባት ከበቂ በላይ መሆነቸውን ተናግረው እኛ ምንም ብንታገስ ከተጠቃን ግን መከላከላችን አይቀርም ሲሉ ማለታቸው ይታወሳል፡፡
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እኛ ብቻ ጦርነትን ማስቀረት አንችልም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ይህን አስመልክቶ በጉዳዩ ላይ ሃሳባቸውን የሰጡት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ ኢዜማ ሊቀመንበር ሙሉዓለም ተገኝ (ዶ/ር) ዳግም ጦርነት እንዳይነሳ እንዲሁም የውጭ ሃይል ጣልቃ ገብነትን ለማስቀረት ድርድር እና ሽምግልናን ጨምሮ ሁሉንም ዓይነት የሰላም ጥረቶች እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረንስ(ኦፌኮ) ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ በበኩላቸው የህዝብን ሃብት እና ወጣቱን አላማ ለሌለው ጦርነት ማዋል በምንም መመዘኛ አግባብነት እንደሌለው ሁለቱም አካላት ማወቅ አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አቶ ሙላቱ ሕወሃትም ሆነ የፌደራል መንግስት ለፈረሙት የሰላም ስምምነት እና ህገ መንግስት መገዛት ፍላጎት ሳይሆን ግዴታ እንደሆነ ማወቅ አለባቸው ሲሉ አክለዋል፡፡
በትናንትናው እለት የፕሪቶሪያን የሰላም ስምምነት ሶስተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ መግለጫ የሰጠው ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች የተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ውጥረቱ በንግግር እንዲፈታ ጠይቋል፡፡
ድርጅቱ በማከልም ህዘቡ ጦርነት እንፈልግም፣ ልጆቻችንንም እንሰጥም በማለት ጦርነቱን እንዲከላከል እና እንዲያወግዝ መክሯል፡፡
ባለፈው ሳምንት ፓርላማ ቀርበው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በመጣስ እና ህገ መንግስቱን ባለማክበር ህወሓትን መክሰሳቸውን ተከትሎ መግለጫ ያወጣው ሕውሃት የፌደራል መንግስት ጦርነት ለማካሄድ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው በሚል መክሰሱ ይታወሳል፡፡
ይህን እንቅስቃሴም አለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያስቆም ጠይቆ ነበር፡፡
ከትናንት በስቲያ በጉዳዩ ላይ መግለጫ ያውጣው የአውሮፓ ህብረት ልዑክ በበኩሉ ሁለቱ አካላት በዚህ ዓመት ይደረጋል ተብሎ ከሚጠበቀው ምርጫ አስቀድሞ የስምምነቱ ፈራሚ አካላት ፖለቲካዊ ንግግር እንዲያደርጉ ጠይቋል፡፡
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
👇👇👇
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s












Comments