top of page

''በገና በዓል ወቅት የሀይል መቆራረጥ እንዳይፈጠር የቅድመ ዝግጅት ስራዬን አጠናቅቄአለሁ'' የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት

  • sheger1021fm
  • 1 day ago
  • 2 min read

ታህሳስ 27/2018


በገና በዓል ወቅት የሀይል መቆራረጥ እንዳይፈጠር የቅድመ ዝግጅት ስራዬን አጠናቅቄአለሁ ሲል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተናገረ።


በበዓሉ እለት እና በዋዜማው የሀይል መቆራረጥ አንዳይኖርም አስቀድሞ የጥገና ስራ እየተሰራ ነው ብሏል፡፡


ከዚህ ቀደም በበዓሉት ወቅት ይፈጠሩ የነበሩ የሀይል መቆራረጦች ለማስቀረት እየሰራ መሆኑን የተናገረው አገልግሎቱ ረቡዕ ታህሳስ 29 ቀን በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በሚከበረው የገና በዓልም ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር አስቀድሜ ስራዎችን ሰርቻለሁ ብሏል።


አገልግሎቱ ይህንን ያለው የገና እና የጥምቀት በዓላትን በማስመልከት በተከናወኑ የቅድመ ዝግጅት ስራዎቹ ላይ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።

ree

የገና በዓል ከሌሎች በዓላት በበለጠ በደንበኞች ዘንድ የሀይል አጠቃቀሙ ክፍተኛ በመሆኑ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተናግሯል።


በዓል ሲደርስ ደንበኞች በተመሳሳይ ሰዓት የኤሌክትሮክ ሀይልን በብዛት የመጠቀም ልምድ አላቸው የተባለ ሲሆን በዚህ ምክንያትም መቆራረጥ ሲከሰት መቆየቱ ተነስቷል።


በዘንድሮ የገና በዓልም ያልተቆራረጠ የኤሌክትሪክ ሀይል ለደንበኞች ለማቅረብ፣ መቆራረጥ ሲከሰትም በአፋጣኝ ምላሽ ለመስጠትም የቅድመ ዝግጅት ስራን አጠናቀናል ሲሉ በአገልግሎቱ የኔትወርክ መሰረተ ልማት ኦፕሬሽን እና ኤክሰለንስ ዳይሬክተር አቶ ፈሪድ አብዱሰላም ተናግረዋል።


በዚህም የመካከለኛና ዝቅተኛ ማሰራጫ መስመሮችን የመፈተሽ፣ የረገቡ የኤሌክትሪክ ገመዶችን የመወጠር፣ የእንጨት ምሰሶዎችን በኮንክሪት የመቀየር፣ የሀይል ጫና ያለባቸውን የትራንስፎርመሮች አቅም የማሳደግ እና አዲስ ወይም አጋዥ ትራንስፎርመሮችን የመትከል ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።


በበዓሉ ዋዜማ እና በዕለቱ የሀይል ፍላጎቱ ከፍተኛ መሆኑን ተከትሎ እጥረት እንዳይፈጠር ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ጋር ውይይት አድርጌ በቂ ሀይል ለማቅረብ ዝግጅቴን አጠናቅቄአለሁ ብሏል።


በሌላ በኩል በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ65,000 በላይ ትራንስፎርመሮች ላይ የምርመራ ስራዎችን ተሰርተው ለኤሌክትሪክ ሀይል መቆራረጥ መንስኤ የሚሆኑ የተለያዩ ግኝቶች ተገኝተዋል ያሉት ዳይሬክተሩ ከዚህም መካከል 40 በመቶ በሚሆኑት ላይ የማስተካከያ ስራዎችን ሰርተናል ብለዋል።


ከመልሶ ግንባታ ጋር በተገናኘም 393 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የመካከለኛ መስመር እና 139 ኪ.ሜ የዝቅተኛ መስመር የመልሶ ግንባታ ስራ ተሰርቶ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኗል መባሉን በመግለጫው ሲነገር ሰምተናል።


በገና ዋዜማ እና በእለቱ የሀይል መቆራረጥ ችግር ሳይፈጠር ለተጠቃሚው ለማቅረብ ከተከሰተም በአፋጣኝ የአስቸኳይ ጥገና ስራ ለመስራት በሀገር አቀፍ ደረጃ ግብረ ሀይል እንዲቋቋም ተደርጓል ያለው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአዲስ አበባ ከተማም 15 የአስቸኳይ ጥገና ቡድኖች ተዘጋጅተዋል ብሏል።


ደንበኞችም የሀይል ጭነት በማይበዛባቸው ሰዓታት በተለይም ከምሽቱ 4:00 እስከ ንጋቱ 11:00 ሰዓት ባለው ጊዜ እንዲጠቀሙ ያለው አገልግሎቱ በተባለው ሰዓት በመጠቀም የተሻለ ኤሌክትሪክ ሀይል ከማግኘት ባለፈ ሊገጥም የሚችልን የሀይል መቆራረጥን ለመቀነስ ይረዳል ብሏል።


ፋሲካ ሙሉወርቅ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page