top of page

በደቡብ ምስራቅ እስያ ይሰሩ የነበሩ ባለሃብቶች በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የታሪፍ ተጽዕኖ ምክንያት መዳረሻቸውን ኢትዮጵያ እያደረጉ ነው ተባለ።

  • sheger1021fm
  • 3 hours ago
  • 2 min read

ጥር 29/2018

 

በደቡብ ምስራቅ እስያ ይሰሩ የነበሩ ባለሃብቶች በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የታሪፍ ተጽዕኖ ምክንያት መዳረሻቸውን ኢትዮጵያ እያደረጉ ነው ተባለ።

 

ኢትዮጵያም ዕድሉን በመጠቀም በተለይ ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተጨማሪ ባለሃብቶችን ከአካባቢው ሀገራት ለመሳብ ጠንክራ እየሰራች እንደምትገኝ ተነግሯል።

 

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢትዮጵያን ጨምሮ አንድ መቶ በሚደርሱና ምርቶቻችውን ወደ አሜሪካ በሚልኩ ሀገራት ላይ ታሪፍ መጣላቸው ይታወሳል።

 

 ትራምፕ ከ10 በመቶ እስከ 54 በመቶ የሚደርስ ታሪፍ ነው በሀገራቱ ላይ የጣሉት።

 

አስር በመቶ ታሪፍ ከተጣለባቸው ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ ፤ ኬንያ፣ ኤርትራ፣ ጅቡቲ፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ይገኙባቸዋል።

 

የደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት የሆኑት ቻይና ፤ ቬትናም ፤ ካምቦዲያ እና ታይላንድ ደግሞ ከፍተኛው ታሪፍ ከተጣለባቸው መካከል ናቸው።

 

ቻይና  54 በመቶ ፤ ካምቦዲያ 49 በመቶ ፤ ቬትናም 46 በመቶ እና ታይላንድ 36 በመቶ ታሪፍ ተጥሎባቸዋል።

 

ትራምፕ፤ በሀገራቱ ላይ ታሪፉን የጣሉት አሜሪካውያን ሸማቾች የአገር ውስጥ ምርቶችን እንዲገዙ እንደሚያበረታታ ተናግረዋል።

 

የአሜሪካንን ኢኮኖሚ እንደሚያሳድገው እና የሚሰበሰበውን ታክስም እንዲጨምረው ጠቅሰዋል።

 

ከፍ ያለ ታሪፍ የተጣለባቸው ሀገራት በኢንቨስትመንት ፍሰታቸው ላይም ተፅዕኖ እያረፈ እንደሚገኝ ተነግሯል።

 

በአንጻሩ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ እና አነስተኛ ታሪፍ የተጣለባቸው ሀገራት በተሻለ መልኩ ኢንቨስትመንት እየሳቡ ነው ተብሏል።

 

በተለይ ከደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ቦታ ይዘው እንዲሰሩ የተጣለው ታሪፍ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ ተጠቅሷል፡፡

 

በተለይ በፀሃይ ሃይል የሚሰሩ መገልገያዎችን የሚያመርቱ ኩባንያዎች ከደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት ይልቅ ኢትዮጵያን እንዲመርጡ እያደረገ ነው ሲሉ፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ሃላፊ አቶ ጳውሎስ በለጠ ነግረውናል።

 

 ከዚህ በኋላም በደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት የነበሩ ተጨማሪ ኢንቨስትመንቶች ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ጳውሎስ ተናግረዋል።

 

ለዚህ ታሪፉ ከፈጠረው ዕድል ባሻገር ኢትዮጵያ ስላላት ምቹ ሁኔታም በስፋት እያስተዋወቅን ነው ብለውናል።

 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከሠሞኑ ከህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ ይህንኑ ጉዳይ አንስተውት እንደነበር ይታወሳል፡፡

 

ከቬትናም የመጣ አንድ የሶላር ኩባንያ ያስገኘው ገቢ ብቻውን በትላልቅ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያሉ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካዎች ተደምረው ካመጡት ይበልጣል ሲሉ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት ሶላር ላይ የሚሰሩ ሌሎች አምስት ፋብሪካዎች መጥተዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚቀጥለው ዓመት በትንሹ፤ 900 መቶ ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የውጭ ምንዛሪ ያስገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።

 

ሶዮ ሶላር የቬትናም ፤ የጃፓን እና የቻይና መሰረት ያለው ግዙፍ ኩባንያ እንደሆነ ተነግሯል።

 

ከአንድ መቶ ሚሊየን ዶላር በላይ ኢንቨስት በማድረግ በሃዋሳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን እየሰራ እንደሚገኝ ነው የተጠቀሰው።

 

ምርቶቹን ወደ መካከለኛው ምስራቅ ፤ ህንድና አሜሪካ እየላከ ነውም ተብሏል።


ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ…..

ንጋቱ ረጋሣ

 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

 

YouTube : https://shorturl.at/18TS1                    

 

Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page