top of page

የኢትዮጵያ የበጀት ጉድለት ከአንድ በመቶ በታች መሆኑ የኢኮኖሚ እድገቱ ላይ ተፅዕኖ እንዳያመጣ ስጋት ይፈጥራል ተባለ፡፡

  • 39 minutes ago
  • 1 min read

ሚያዝያ 7/2018


የኢትዮጵያ የበጀት ጉድለት ከአንድ በመቶ በታች መሆኑ የኢኮኖሚ እድገቱ ላይ ተፅዕኖ እንዳያመጣ ስጋት ይፈጥራል ተባለ፡፡


ባለፈው 7 ወር የበጀት ጉድለቱ ከአጠቃላይ ሃገራዊ ምርቱ ጋር ሲመሳከር 0.7 በመቶ መድረሱን የብሔራዊ ባንክ መረጃ ያሳያል፡፡


በብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴው በቅርቡ ያወጣው መረጃ ነው ይህን ያሳየው፡፡


በጉዳዩ ላይ ሸገር ያነጋገራቸው የምጣኔ ሐብት ተንታኙ አቶ ዋሲሁን በላይ የበጀት ጉድለት እስከ 3 በመቶ እንዲሆን የምጣኔ ሐብት ሳይንሱ ይመክራል ብለዋል፡፡



እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አዳጊ ሀገራት ደግሞ ጉድለቱ እስከ 5 በመቶ ቢሆንም አይከፋም ይላሉ፡፡


ይህም መንግስት ከሚያገኘው ገቢ በላይ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳርግበትን ወጭ እያወጣ ፕሮጀክቶች ላይ ፈሰስ ማድረግ ስላለበት የሚሰጥ ምክር ነው ብለዋል፡፡


ቁጥሩ ከ1 በመቶ በታች ማነሱ ግን የመንግስት ወጭ ምን ያህል የተገደበ እንደሆነ ያሳያልና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን እንዳያቀዛቅዘው ስጋት ይፈጥራል ብለዋል፡፡


የበጀት ጉድለቱ እንዲህ ዝቅተኛ መሆኑ የዋጋ ግሽበቱ በቁጥር እንዲቀንስ ሊያደርገው ይችላል ያሉት አቶ ዋሲሁን በተግባር ግን የመንግስትን እጅ የሚጠብቁ ምርታማነትን የሚያሳድጉ ፕሮጀክቶች እንዲቀዛቀዙ ፣ ሊያደርግ ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ተናግረዋል፡፡


በሌላ በኩል የመንግስት ወጭ ከአምናው አንፃር በ48 በመቶ ከፍ ማለቱን የፖሊሲ ኮሚቴው ያወጣው መረጃ ጠቁሟል፡፡


ይህ ግን የመንግስት ገቢ ከፍ ባለበት ምጣኔ ልክ ያደገ ወጭ አይደለም የሚሉት ባለሙያው የመንግስት ወጭ ከፍ ያለው ለምን ጉዳይ ወጭ ሆኖ ነው የሚለውን መመርመርም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡


ኢትዮጵያ አሁንም ባልበረዱ የእርስ በርስ ጦርነቶች ውስጥ መሆኗ ይታወቃል፡፡


በመሆኑም ወጭዎቹ ለፍጆታ ፣ ለጦርነት ፣ ለድጎማ እና መሰል ጉዳቶች የሚውል ከሆኑ ጤናማ አይደለም የሚሉት ባለሙያው አዳጊ ሃገራት የበጀት ጉድለታቸው እስከ 5 በመቶ እንዲደርስ የሚመከረው ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ፕሮጀክቶችን በማብዛት የስራ እድል እንዲፈጥሩ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴያቸውን እንዲያበረቱ ስለሚያስፈልግ ነው ብለዋል፡፡


ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ…..


ትግዕስት ዘሪሁን

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page