በዓለም አቀፍ ገንዘብ ድርጅት 32 ዓመት በተለያየ የስራ ሀላፊነት ያገለገሉት ኢትዮዽያዊው አበበ አዕምሮ ሥላሴ በጡረታ ሊገለሉ እንደሆነ ተሰማ
- sheger1021fm
- 4 hours ago
- 1 min read
ታህሳስ 30/2018
በከፍተኛ ደረጃ በኢኮኖሚ ባለሞያነት፣ በዓለም አቀፍ ገንዘብ ድርጅት (IMF) 32 ዓመት በተለያየ የስራ ሀላፊነት ያገለገሉት ኢትዮዽያዊው አበበ አዕምሮ ሥላሴ፤ ከ3 ወር በኋላ በጡረታ ሊገለሉ እንደሆነ ተሰማ።
አቶ አበበ በዓለም አቀፍ ገንዘብ ድርጅት IMF ከ 30 ዓመት በላይ በተለያየ ኃላፊነት ፣ የባለፉትን 10 ዓመታት ደግሞ የአፍሪካ ዳይሬክተር ሆነው እያገለገሉ ነው።
በማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ቀረፃ እና ትንተና፣ በፋይናንስና በገንዘብ ነክ ፖሊሲ ጉዳዮች፣ በዕዳ ሽግሽግ፣ አጠቃላይ በገንዘብ ቁጥጥር እና ፊስካል ፖሊሲ ሰርተዋል።

የ IMF ዋና ዳይሬክተር፣ ክሪስታሊና ጆርጂየቫ፣ አበበ አዕምሮ ስላሴ ከአፍሪካ ዲፓርትመንት ዳይሬክተርነት ከ3 ወር በኋላ ይገለላሉ ብለዋል።
ከ2008 ጀምሮ በIMF አፍሪካ ክፍል ዳይሬክተር ሆነው ያገለገሉት አበበ አዕምሮ፤ በተለይ ከኮቪድ ወረርሽኝ፤ በግጭት እና አለመረጋጋት እና ሌሎች ፈተናዎች ወቅት አፍሪካ ከድርጅቱ ጋር ባላት የገንዘብ ነክ እና ጥልቅ ማክሮ ኢኮኖሚ ጉዳዮችን መርተዋል።
ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘም በአለም ባጋጠመው ግዙፍ የአኢኮኖሚ መነቃነቅ እና ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት፤ አፍሪካን መፈተኑን ተከትሎ የተለያዩ ፖሊሲዎችን እና አጋዥ ኢኮኖሚያዊ ውሳኔዎችን እና ምክሮችን አቀብለዋል።
በተለይ ከሳህራ በታች ያሉ አፍሪካ ሀገሮች ከሀገራቸው ሁኔታ ጋር የሚስሙማ የፖሊሲ ምክር ሰጥተዋል።
በእዳ ጫና ኢኮኖሚያቸው የተፈተኑ ሀገሮች፣ በግጭት እና ጦርነት የታመሱ የአፍሪካ ሀገሮችን ለመደገፍ እና በተሰጣቸው ኃላፊነት መሰረት ለሀገሮቹ ተጨማሪና የተመደበው እርዳታ እንዲሰጣቸው አግዘዋል።
ዳይሬክተፘ ክሪስታሊና ፤ ኢኮኖሚስቱ አበበ አምሮ IMF ለቀረፃቸው እርዳታዎችና ፖሊሲዎች ፤ በማስፈፀም ረገድ ታማኝነታቸውን በማሳየታቸው አመስግነዋቸዋል።
አቶ አበበ፤ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት IMF ለሚቀርፀው ፕሮግራሞች ላይ በተለያዩ ሀገሮች፤ በከፍተኛ ኢኮኖሚ ሞያ እና ምክር አገልግለዋል።
ተህቦ ንጉሴ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
Telegram : https://t.me/ShegerFMRadio102_1
Facebook፡ https://web.facebook.com/Sheger102.1








