top of page

በኢትዮጵያ ከሚወለዱ 10,000 ህጻናት 83 ቱን የሚያጠቃው የነርቭ ዘንግ የአፈጣጠር ችግር

  • sheger1021fm
  • Nov 14, 2025
  • 3 min read

ህዳር 5 2018


በኢትዮጵያ ከሚወለዱ 10,000 ህጻናት 83 ቱን የሚያጠቃው የነርቭ ዘንግ የአፈጣጠር ችግር


በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ30,000 - 50,000 ህጻናት ከነርቨ ዘንግ የአፈጣጠር ችግር (Spina Bifida) ጋር ይወለዳሉ፡፡


በዚህም ምክንያት አብዛኞቹ ሕጻናት ለዕድሜ ልክ የአካል ጉዳት አለፍ ሲልም ለሞት ይዳረጋሉ፡፡


የነርቭ ዘንግ የአፈጣጠር ችግር ምንድነው?


ስፓይና ቢፊዳ (Spina bifida) ማለት ከነርቨ ዘንግ የአፈጣጠር ችግሮች ውስጥ አንዱ ሲሆን የአከርካሪ አጥንትና የህብለሰረሰር በአግባቡ አለመዘጋት(ክፍተት) ነው። በአብዛኛው ጊዜ ስፓይና በፊዳ ያለባቸው ሕጻናት ፈሳሽ በአጎላቸው ወስጥ ስለሚከማች ሃይደሮ ሴፋለስም ያጋጥማቸዋል።


ሃይድሮ ሴፋለስ ምንድነው?


ሃይድሮ ሴፋለስ ማለት በጭንቅላት ውስጥ ከመጠን በላይ የፈሳሽ ክምችት ሲሆን ይህም የአዕምሮ ግፊት እንዲጨምርና የራስ ቅል ላይ መለጠጥ ሊያስከትል ይችላል።


የነርቭ ዘንግ የአፈጣጠር ችግር ወይም ስፓይና ቢፊዳ ጋር የተወለዱ ልጆች ምን ምልክቶች አሉባቸው?


ጠቅላላ ሀኪም እና በሆፕ ኤስ ቢ ኤች የፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት ነብዩ ሁሴን(ዶ/ር)፤ ህጻናት ገና ሳይወለዱ በእርግዝና ክትትል ወቅት የነርቭ ዘንግ የአፈጣጠር ችግር ይኑርባቸው አይኑርባቸው ማወቅ አንደሚቻል ነግረውናል፡፡ ቀድሞ ማወቁ እንደተወለዱ ከ24 እስከ 48 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ በቀዶ ህክምና የነርቭ ዘንግ ክፍተቱን መዝጋት ይቻላል ሲሉም ያስረዳሉ፡፡



ልጆቹ በሽታው አንዳለባቸው በሚከተሉት ምልክቶች ማወቅ ይቻልል፤


➡️ በአከርካሪ አጥንት የታችኛው ክፍል ላይ የሚከሰት እብጠት(ክፍተት ቁስለት)

➡️ የአንጀት እና የሽንት ፊኛ ችግሮች(ሽንትና ሰገራ መቆጣጠር አለመቻል)

➡️የእግር እና እጅ የማንቀሳቀስ ችግሮች

➡️የተቆለመመ እግር

➡️የዳሌ አጥንት ራስ ከቦታ መልቀቅ፡፡


ሃይድሮ ሴፋለስ ወይም በጭንቅላት ውስጥ ከመጠን በላይ የፈሳሽ ክምችት ያለባቸው ህጻናትስ ምን ምልክቶች ያሳያሉ?


➡️ፈጣን የጭንቅላት አድገት፣ የፊተኛው አርግብግቢት መወጠር

➡️የዓይን ሁልጊዜ ወደታች መመልከት

➡️እንቅልፍ ማጣት

➡️የአዕምሮ ዝግመት

➡️ዓይነ ስውርነት

➡️የመስማት ችግር


በነርቭ ዘንግ የአፈጣጠር ችግር የተጠቁ ህጻናት ከተወለዱ ምን መደረግ አለበት?


➡️የነርቭ ዘንግ ክፍተት እና የጭንቅላት ውስጥ ፈሳሽ ከመጠን በላይ ክምችት ምልክቶች በህጻናት ላይ ካስተዋሉ በአስቸኳይ ወደ ጤና ተቋማት መውሰድ ያስፈልጋል፣

➡️ህይወታቸውን የሚያደኑ እና የሚያሻሽሉ የህክምና አማራጮች መኖራቸውን መረዳት፣

➡️በበሽታው ምክንያት የአካል ጉዳተኛ የሚሆኑ ህጻናት እና ወጣቶች አካታች የሆኑ አከባቢዎች በማመቻቸት ስራዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡



ከነርቨ ዘንግ የአፈጣጠር ችግር (ስፓይና ቢፊዳ) ዋና ዋና መንስኤዎች ምንድን ናቸው?


የስፓይና ቢፊዳ ችግር በዋነኛነት እናቶች በእርግዝና ወቅት የፎሊክ አሲድ አጥረት ሲያጋጥማቸው ይፈጠራል፡፡ይህም አስከ 70 በመቶውን ምክንያት ይወስዳል፡፡


ከዚህ በተጨማሪም እናቶች በእርግዝና ወቅት ባሉባቸው ተጓዳኝ የጤና ችግሮች ምክንያት ለምሳሌ የስኳር በሽታ፣ ከመጠን በላይ ውፍረት ያለባቸው እናቶች የሚወልዷቸው ልጆች ስፓይና ቢፊዳ ተጋላጭ ናቸው፡፡

በእርግዝና ወቅት እናቶች ለሌሎች በሽታዎች የሚወስዷቸው መጽኃኒቶች (ለምሳሌ ለሚጥል በሽታ) ምክንያት ሊከሰት እንደሚችል ጥናቶችን ጠቅሰው ጠቅላላ ሀኪም እና በሆፕ ኤስ ቢ ኤች የፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት ነብዩ ሁሴን (ዶ/ር) ነግረውናል፡፡


ህጻናት ከነርቨ ዘንግ የአፈጣጠር ችግር (ስፓይና ቢፊዳ) አንዳይጋለጡ ምን ማድረግ ያስፈልጋል?


➡️አንዲት ሴት እድሜዋ ከ 15-49 በሚሆንበት ጊዜ በተፈጥሮ ፎሊክ አሲድ የያዙ ምግቦችን ለምሳሌ ምስር፣ ሰላጣ፣ አቮካዶ፣ አተር እና የዶሮ ስጋ መመገብ አለባት፣

➡️ከእርግዝና በፊት ለሶስት ወራት እና እርግዝና ከተፈጠረ ብኋላ ለ3 ወር የፎሊክ አሲድ እንክብሎች በየቀኑ መውሰድ

➡️በፎሊክ አሲድ የበለፀጉ ምግቦችን ለምሳሌ በፎሊክ አሲድ የበለፀገ የስንዴ ዱቄትና ዘይት በመመገብ በሽታውን መከላከል ይቻላል።


የነርቨ ዘንግ የአፈጣጠር ችግር ያለባቸውን ህጻናትን የት ማሳከም ይቻላል? ተጎጂዎችን የሚያግዙ ተቋማትስ አሉ ወይ?


በአዲስ አበባ ያሉትን ዘውዲቱ፣ ቅዱስ ጴጥሮስ፣ የካቲት 12 ሆስፒታሎችን ጨምሮ በ12 የመንግስት ሆስፒታሎች ህክምናው ይሰጣል፡፡

ሆፕ ኤስ.ቢ.ኤች (HOPE-SBH) የተባለ የነርቭ ዘንግ ክፍተትና የጭንቅላት ውስጥ ከመጠን በላይ የፈሳሽ ክምችት ያለባቸው ህጻናት ላይ የሚሰራ ሀገር በቀል ግብረሰናይ ድርጅት አለ::


ድርጅቱ ችግሩ ትኩረት እንዲያገኝ ማድረግ አንዲሁም በችግሩ የተጠቁ ህጻናት እና ቤተሰቦች ህክምና እና አንክብካቤ እንዲያገኙ እንደሚሰራ ነግሮናል፡፡

እስከ አሁን  ከ5,700 በላይ ቤተሰቦችን ከሀገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች ለቀዶ ህክምና አገልግሎት ወደ አዲስ አበባ ለሚመጡ ህጻናት እና ቤተሰቦች ማቆያ ቦታ በማዘጋጀት፣ በቅድመ እና ድህረ ቀዶ ህክምና ወቅት የመጠበቂያ እና ማገገሚያ ስፍራ ያዘጋጃል፡፡

 

ለችግሩ ተጠቂ ለሆኑ ህጻናት ሽንትና ሰገራ እንዴት መቆጣጠር አንደሚችሉ ስልጠና  መስጠትን ጨምሮ ሎሎች በርካታ ስራዎችን አንደሚሰራ የድርጅቱ መስራች ወ/ሮ ቤዛ በሻህ ተናግረዋል፡፡


ወ/ሮ ቤዛ በሻህ ድርጅቱን የመሰረቱት ሁለተኛ ልጃቸው የበሽታው ተጠቂ ሆኖ በ7 ዓመቱ ከዚህ አለም በሞት መለየቱን ተከትሎ ግንዛቤ ለመፍጠር በማሰብ መሆኑን ስለ በሽታው ግንዛቤ ለመፍጠር ድርጅታቸው ባሰናዳው ፕሮግራም ላይ ተናግረዋል፡፡


ንጋቱ ሙሉ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

👇👇👇


Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page