top of page

በኢትዮጵያ ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚሆን የሰብል ምርት በማከማቻ ችግር ምክንያት እንደሚባክን ይነገራል።

  • sheger1021fm
  • 58 minutes ago
  • 2 min read

ጥር 25/2018

 

በኢትዮጵያ ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚሆን የሰብል ምርት በማከማቻ ችግር ምክንያት እንደሚባክን ይነገራል።

 

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ አሁን ላይ ያላት የሰብል ማከማቻ 4 ነጥብ 8 ሚሊየን ቶን መያዝ የሚችል ነው።

 

78 በመቶው ዘመናዊ ማከማቻ ነው የተባለ ሲሆን ቀሪው እንደ ቆርቆሮ ባሉ ቁሳቁሶች የተገነባ  እንደሆነ ተጠቅሷል።

 

ችግሩ የኢትዮጵያ የሠብል ምርት በአለም አቀፍ ገበያ ባለው ተወዳዳሪነት ላይም ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ ይነሳል።

 

ወደፊት ደግሞ ምርቱ እየጨመረ መሄዱ ስለማይቀር ለማከማቸት ስለሚያስፈልገው መጋዘን ከወዲሁ ማሰብ ይገባል የሚሉ ብዙ ናቸው።

 

በረጅም ጊዜ ብክነቱ ከአምስት በመቶ በታች እንዲሆን የሚያስችል ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ መሆን እንደጀመረ በመንግስት በኩል ተነግሯል።

 

ችግሩ በዜጎች የምግብ ዋስትና ላይም የጎላ ተፅዕኖ እንዳለው በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ ተወካይ አቶ ተሾመ ገለቱ ይናገራሉ።

 

አሁን ላይ ከብረት እና አልሙኒየም የሚሰሩ የሠብል ማከማቻዎችን አርሶ አደሩ በስፋት እንዲጠቀም እየተሰራ እንደሆነ የነገሩን አቶ ተሾመ ፤ ለነቀዝ እና ሌሎች ነብሳት የማይጋለጡ ማዳበሪያዎችን እና ኬሻዎችን እንዲያገኝም እያደረግን ነው ብለውናል።

 

ራሱ አርሶ አደሩም ጎተራዎችን በኮንክሪት ሰርቶ እንዲጠቀም ድጋፍ እየተሰጠ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።

 

የአለም ባንክ እና የሮክፌለር ፋውንዴሽን ከሠሞኑ ይህንኑ የምርት ብክነት ለመቀነስ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ስራ ላይ እንዲውል ለማገዝ 50 ሚሊየን ዶላር ገንዘብ መስጠታቸው ተሠምቷል።

 

ቴክኖሎጂው በፀሃይ ሃይል የሚሰሩ የምርት ማከማቻ ማቀዝቀዣዎችን ለአርሶ አደሮች የሚያስተዋውቅ እንደሆነ ተነግሯል።

 

ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በኬንያ ፤ ናይጄሪያ ፤ ሴራሊዮን ፤ ዩጋንዳ እና ኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ እንዲተገበር የታሰበ መሆኑም ተጠቅሷል።

 

ስለዚሁ የጠየቅናቸው አቶ ተሾመ ስለፕሮጀክቱ ለጊዜው መረጃ እንደሌላቸው ነግረውን፤ የሠብል ምርት ብክነትን ለመቀነስ ግን ፤

 ከሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በትብብር እየሰራን ነው ብለውናል።

 

ከማከማቻ ውጪ በማጨድ ፣ በመከመር፣ በመውቃት እና በማጓጓዝ ሂደትም የሠብል ምርት እንደሚባክን የሚናገሩት አቶ ተሾመ ፤

ግብርናን ሜካናይዝድ ወደ ሆነ አሰራር በመቀየር ችግሩን ለመቀነስ ስራ መጀመሩን አክለዋል።

 

በአለም አቀፍ ደረጃ በመሰብሰብ ሂደት 800 ሚሊየን ሰዎችን መመገብ የሚችል የግብርና ምርት እንደሚባክን መረጃዎች ያሳያሉ።

 

በአፍሪካም በዚሁ ምክንያት ከሚመረተው ሰብል 30 ከመቶ በላዩ እንደሚባክን ተጠቁሟል።

 

278 ሚሊዮን የሚሆን የአህጉሪቱ ሕዝብ በዚሁ በድህረ ምርት ብክነት ምክንያት የረሃብ አደጋ ያጋጥመዋል ተብሏል፡፡

 

ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ…..

 

ንጋቱ ረጋሣ

 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

 

YouTube : https://shorturl.at/18TS1                   

 

 

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page