በኢትዮጵያ እና ኬንያ ድንበር አካባቢ ያለ ህዝብ በመጪው ዓመት ከባድ የድርቅና ረሃብ ስጋት ተጋርጦበታል ተባለ።
- sheger1021fm
- Nov 25
- 2 min read
ህዳር 16 2018
ቦረናን ጨምሮ 85 በመቶ የሚሆነው በኢትዮጵያ እና ኬንያ ድንበር አካባቢ ያለ ህዝብ በመጪው ዓመት ከባድ የድርቅና ረሃብ ስጋት ተጋርጦበታል ተባለ።
በኢትዮጵያ እና ኬንያ ድንበር ቦረና ኢትዮጵያ እና ማርሳቢት ኬንያ አካባቢ ዝናብ አጠር መሆኑና አልፎ አልፎ ሲዘንብም ጎርፍ የሚያስከትል መሆኑ ተነግሯል፡፡
ይህ የተባለው ቮለንተሪ ሰርቪስ ኦቨር ሲስ(VSO)፣ ሆርን ኦፍ አፍሪካ ዴቨሎፕመንት ኢንሼቲቭ (HODI) ፣አውስትራሊያን ዴቨሎፕመንት ኮፕሬሽን እና ሴንተር ፎር ዴቨሎፕመንት ኤንድ ጉድ ገቨርነንስ የተሰኙ የሲቪል ማህበራት በአካባቢው ሲሰሩ የቆዩትን የመጀመሪያ ዙር ፕሮጀክት ለመዝጋት በጋራ ባሰናዱት መድረክ ላይ ነው።
የVSO የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ተመስገን አለሙ የአትዮጵያ ኬንያ ድንበር ከግጭት፣ ከድርቅ እና ረሃብ ባለፈ አካባቢው የአደንዛዥ ዕፅ ፣ ህገ-ወጥ የሰው ዝውውር እና ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃት የበዛበት አካባቢ ነው ብለውናል።
የሲቪል ማህበር ተወካዩ ቦረናና የኢትዮ ኬንያ ድንበር አካባቢ ያለውን የድርቅ፣ የግጭት እና እሱን ተከትሎ የሚመጣውን ረሃብ መንስኤ እና መፍትሔ በጥናት ለመንግስት አቅርበናል ብለዋል።
ሴንተር ፎር ዴቨሎፕመንት ኤንደ ጉድ ገቨርነስ ቦርድ ሰብሳቢና የኦሮሚያ ግብርና ምርምር አማካሪው አቶ አበራ ዴሬሳ በቦረና እና በኬንያ ድንበር አካባቢ ያለውን የድርቅ፣ የግጭት፣ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን ለማስቀረት መንግስት የፖሊሲ አማራጮችን እንዲከተል መክረዋል፡፡
ባለሙያው በተለይ በኬንያና ኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ በሚደረግ የቤት እንሰሳት ዝውውር ድርቁን ተከትሎ ሪፍት ቫሊ ፊቨር የእንሰሳት በሽታ ከተከሰተ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ሃገር የምትልከው ስጋ የሚታገድበት አጋጣሚ ሊኖር እንደሚችል አስረድተዋል፡፡
ሴንተር ፎር ዴቨሎፕመንት ኤንድ ጉድ ገቨርነስ ቦርድ ሰብሳቢና የኦሮሚያ ግብርና ምርምር አማካሪው አቶ አበራ ዴሬሳ ቦረና ከሁለት አመት በፊት በተከሰተ ድርቅ ከሁለት ሚሊየን በላይ የቤት እንሰሳት ሞተው ነበር ያሉ ሲሆን መንግስት የከርሰ ምድር ውሃን ማዘጋጀት ላይ እንዲያተኩር መክረዋል፡፡
የሲቪል ማህበራቱ የኢትዮጵያ እና የኬንያ የመንግስት አካላት በአካባቢው ያለውን ችግር ለማስቆም ከአሁኑ የተሻለ እና ተቋማዊ የሆነ ሥራ እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
ባለሙያው ድርቅ በሚመጣበት ወቅት የአካባቢው አርብቶ አደሮች ከብቶቻቸውን ለመሸጥ ፍቃደኛ አለመሆናቸው ድርቁ የሚያመጣውን ጉዳት ለመቀነስ በሚሰራው ስራ ላይ አንዱ እንቅፋት መሆኑን አንስተዋል፡፡
በድርቅ እና በግጭት ምክንያት በአትዮጵያና ኬንያ ድንበር አካባቢ ካሉ ሰዎች፣ 70 በመቶው በድህነት ውስጥ ያለ ነው ተብሏል።
የሲቪል ማህበራቱ የኢትዮጵያ እና የኬንያ የመንግስት አካላት በአካባቢው ያለውን ችግር ለማስቆም ከአሁኑ የተሻለ እና ተቋማዊ የሆነ ሥራ እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
ንጋት መኮንን
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
👇👇👇
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s











Comments