top of page

በኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ለጋሾች ድጋፍ መቀነስ በኤችአይቪ መከላከልና ህክምናው ላይ እያሳደረ ያለው ተፅዕኖ

  • sheger1021fm
  • 5 hours ago
  • 2 min read

ህዳር 24 2018

 

በኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ለጋሾች ድጋፍ መቀነስ ምክንያት በኤችአይቪ መከላከልና ህክምናው ላይ ተጽዕኖ እንዳይበረታ ካልተሰራ የበሽታውን መከላከል ስራ ወደኋላ እንዳይመልሰው ያሰጋል ተባለ፡፡

 

ለዚህም በመንግስት እንዲሁም በአገር በቀል ድርጅቶች በኩል የሚሰራው ስራ መጠናከር እንዳለበት ተነግሯል፡፡

 

የአለም ኤድስ ቀን በኢትዮጵያ እየታሰበ ነው፤ የዘንድሮ ቀን የሚታሰበው ደግሞ ችግሮችን በመቋቋም የኤችአይቪ ኤድስ ( #HIV_AIDS ) ምላሽ ዘላቂነት ማረጋገጥ ላይ አተኩሮ ነው ተብሏል፡፡

 

የዓለም አቀፍ ድርጅቶች የድጋፍ መቀነስ በተለይም የበሽታው መከላከል ላይ ተጽእኖ ከዚህ በላይ እንዳይሰፋ የሀገር ውስጥ ሀብት በማሰባሰብ አገልግሎቶች እንዳይቋረጡ ማድረግ ላይ መሠራት እንዳለበት የተነግሯል፡፡

 

በኢትዮጵያ በድጋፍ ላይ የሚሰሩት ዩኤን ኤድስን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት የዓለም ኤድስ ቀንን አስመልክቶ ባሰናዱት አውደ ጥናት ላይ ነው እንዲህ የተባለው፡፡

 

ሀገራት የሚከውኗቸው የኤች አይ ቪ ፕሮግራሞች በአብዛኛው በበጎ አድራጎት ድርጅቶች ድጋፍ ሲሰሩ የቆዩ መሆናቸውን የሚናገሩት የኤድስ ሄልዝ ኬር ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶ/ር መንግስቱ ገ/ሚካኤል ኤች አይ ቪን ለመከላከልና ህክምናው የሚጠይቀው በጀት ከፍተኛ መሆኑ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ ሀገራት በእርዳታ ላይ ጥገኛ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል ይላሉ፡፡

 

ree

በእርዳታ መቀነስ ምክንያት ሁሉም አገሮች በብዙ ፕሮግራሞች ተቸግረው ይገኛሉ፤ በተለይ ደግሞ ወደ ኤች አይ ቪ ፕሮግራሙ ስንመጣ ከረጅም ጊዜ አንስቶ በአብዛኛው በጎ አድራጎት ድርጅቶች አገሮች ላይ የተንጠለጠለ ፕሮግራም ነው ብለዋል፡፡

 

ይህም የሆነው ለፕሮግራም የሚያስፈልጉ ግብዓቶች፣ የተለያዩ የሰለጠነ ሰው ኃይልም በተለይ ደግሞ መድኃኒት ከዛ ጋር የተያያዙ መመርመሪያ መሳሪያዎች ኤች አይ ቪን ለመከላከል የሚጠቅሙ ግብአቶች የሚያስፈልጋቸው የፋይናንስ መጠን በጣም እጅግ ከፍተኛ ስለሆነ አገራት በተለይም ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ወይም ደግሞ አፍሪካ ውስጥ ያሉ ታዳጊ አገራት ይህንን በራሳቸው ኘሮግራም ለማድርግ በጣም ይቸገራሉ፤ በዛ ምክንያት ለዓመታት እስካሁንም ድረስ የኤች አይ ቪ ፕሮግራም አገሮች ራሳቸውን ችለው የሚሰሩት አልሆንምም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

 

የኤች አይ ቪ የመከላከልና ህክምና ፕሮግራሞች በአብዛኛው በአሜሪካ መንግስት ሲደረግ መቆየታቸውን የሚናገሩት ዶክተር መንግስቱ የእርዳታ መጠኑ በቅርቡ እጅግ መቀነሱ በተለይ የምርመራና ሌሎች ቅድመ መከላከል ላይ ያሉ ስራዎች ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል ብለዋል፡፡

 

በለጋሽ ድርጅቶች ድጋፍ መቀነስ ምክንያት በኤች አይ ቪ ኤድስ አገልግሎቶች ላይ የተለያዩ ተጽዕኖዎች ማሳደራቸው ተነግሯል፡፡

 

የጸረ ኤች አይ ቪ መድኃኒት አቅርቦቱ ላይ ያለው ሀገራዊ ሁኔታስ ምን ይመስላል? ያልናቸው ዶክተር መንግስቱ አብዛኛው ድጋፍ ከአሜሪካ ይሁን እንጂ መድኃኒቱ የሚገዛው በግሎባል ፈንድ ነው መድሀኒት እስካሁን ድረስ እጥረት አላጋጠመም እስካሁን ድረስ እንግዲህ ሙሉ ለሙሉ መድኃኒቱን እያገኙ ነው ተጠቃሚዎቹ፤ በሁሉም ተቋማት የሚቀርቡት በመንግስት ነው ሲሉ መልሰዋል፡፡

 

ኤች አይ ቪን ጨምሮ በሌሎች ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ምክንያት ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ኢትዮጵያውያን የሚደረጉ ዓለም አቀፍ የእርዳታ መጠኖች እየቀነሱ በመምጣታቸው የሀገር ውስጥ ሃብት ማሰባሰብ እና ሀገር በቀል የሆኑ መልሰው ጥቅም የሚሰጡ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተነግሯል፡፡

 

ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ…

ምህረት ስዩም

 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

👇👇👇

Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page