top of page

በኢትዮጵያ በትራፊክ አደጋ ምክንያት የሚደርሰው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር አሁንም ከፍተኛ ሆኗል ተባለ።

  • sheger1021fm
  • Nov 13, 2025
  • 2 min read

ህዳር 4 2018 

 

በኢትዮጵያ በትራፊክ አደጋ ምክንያት የሚደርሰው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር አሁንም ከፍተኛ ሆኗል ተባለ።

 

ላለፋት 15 አመታት በኢትዮጵያ በተለይም በአዲስ አበባ የመንገድ ትራፊክ አደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስና መንስኤዎቹን ለመለየት እየሰራ መሆኑን ብሉምበርግ ፊላንትሮፒስ የተባለው አለም አቀፍ ተቋም ተናግሯል።

 

ተቋሙ ከጆን ሆፕኪንስ ዩንቨርስቲና ከአዲሰ አበባ ዩኒቨርስቲ የህብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት ጋር በመሆን በመንገድ ትራፊክ አደጋ መንስኤዎች እና መፍትኤ ላይ ባሰናዱት አውደ ጥናት ነው ይህን የሰማነው።

 

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት ከተቋማቱ በሚያገኘው ድጋፍ በፍጥነት፣ የደህንነት ቀበቶ አጠቃቀም፣ የሞተር ብስክሌት ቆብ አጠቃቀምና ጠጥቶ ማሽከርከር ላይ ችግሮችን በመለየት የመንገድ ትራፊክ አደጋዎችን ለመቀነስ ጥናቶች ሲከውን መቆየቱ  ተናግሯል።

 

እስካሁን በተሰሩ ጥናቶችም ዋነኛው የትራፊክ አደጋ መንስኤ ፍጥነት መሆኑ ተለይቷል ተብሏል።

 

በሌላ በኩል እግረኞችም የመንገድ አጠቃቀም ችግር የሚታይበት ነው ተብሏል።

 

አብዛኛዎቹ እግረኞች የሚቆጣጠር ወይም የሚገድብ መላ ከሌለ በስተቀር የመንገድ ሥርዓቱን አክብረው አይጠቀሙም ብሏል ጥናቱ።

 

ይህም በትራፊክ አደጋ ምክንያት ቀዳሚ ተጎጂ እንዲሆኑና በአደጋው ምክንያትም የሚደርሰው ማህበራዊም ይሁን ኢኮኖሚያዊ ጫና ከፍተኛ እንዲሆን አድርጓል ተብሏል።

 

በተጨማሪም አሽከርካሪዎች በሚያሽከረክሩበት ወቅት የተንቀሳቃሽ ስልክ አጠቃቀም ችግር መጨመርና ጠጥቶ ማሽከርከር ሌሎቹ የአደጋ መንስኤዎች ናቸው ተብሏል።

 

በተለይ ጠጥቶ ማሽከርከር ጋር ያለው ህግ ከኮቪድ ወረርሽኝ በኋላ ጠበቅ ብሎ እየተሰራበት አለመሆኑ ችግር ነው አሁንም ሊታይ እንደሚገባ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት ተመራማሪ የሆኑት ፕርፌሰር ዋቅጋሪ ዴሬሳ ተናግረዋል።

 

የንግድ እና ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች በፍጥነት ምክንያት ለሚደርሱ አደጋዎች ቀዳሚዎቹ ናቸውም ብለዋል።

 

ከቅርብ አመታት ወዲህ ደግሞ እንደ ሜትር ታክሲ አገልግሎት እና መልዕክት አድራሽነት ጋር ያሉ ስራዎች መስፋፋት እያሽከረከሩ የተንቀሳቃሽ ስልክ በመጠቀም ለሚደርሱ አደጋዎች አንድ መንስኤ መሆናቸውን በከተማዋ የተጠና ጥናት አሳይቷል።

 

ችግሮቹ በየጊዜው እየተለዩ በጥናት ተደግፈው ቢቀርቡም የቁጥጥር ሥርዓቱን ማጥበቅ በተለይ ዋነኛ የአደጋ መንስኤ የሆነው ፍጥነት ላይ መስራት ይጠበቃል ተብሏል።

 

ብሉምበርግ ፊላንትሮፒስ በመንገድ ደህንነት ላይ ለመስራት ከመረጣቸው የአፍሪካ ከተሞች አንዷ አዲስ አበባ ስትሆን ባለፋት 15 አመታት በመንገድ ደህንነት ላይ ለሚከወኑ ጥናቶች ድጋፍ በማድረግና ማሻሻያ የሚጠይቁትን ለመንግሥት ግብዓት በመስጠት ሲደግፍ መቆየቱን ሰምተናል።

 

ምህረት ስዩም

 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

👇👇👇

 

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page