በኢትዮጵያ በሰብአዊ ድጋፎች ላይ የሚከወኑ ስራዎችን የሚደግፉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተሳትፎ የቀነሰ ነው፡፡
- sheger1021fm
- Nov 19
- 2 min read
ህዳር 9 2018
በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ሰብአዊ ድጋፎች ላይ የሚከወኑ ስራዎችን የሚደግፉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ የቀነሰ ነው፡፡
በዚህም ሀገሪቱ ፊቷን ሀገር በቀል ወደሆኑና በራስ አቅም ዘላቂ ድጋፍ ወደ ሚገኝበት መንገድ እያዞረች መሆኑ ተነግሯል።
በኢትዮጵያ በተቀናጀ መንገድ የሰብአዊ እርዳታ ለማድረግ የሚያስችል ጥምረት ተመስርቷል።
በተለያዩ የድጋፍ ዘርፎች ላይ የሚሰሩ 20 ሀገር በቀል የእርዳታ ድርጅቶች የመሰረቱት ''the consortium of humanitarian actors for national grow empowerment'' ወይም CHANGE የሚል ስያሜ የተሰጠው ጥምረቱ ዛሬ በስካይላይት ሆቴል ይፋ ሆኗል፡፡

የሰብአዊ ድጋፍ ስራዎችን ሀገር በቀል በሆኑ ተቋማት መስራት በተለይም የሰብአዊ እርዳታ የሀገር ጥቅምን በማይጎዳ መልኩ እንዲከወን የሚያግዝ ነው ሲሉ የነገሩን የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነሩ አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም ናቸው፡፡
ከዚህ ቀደም በዓለም አቀፍ ተቋማት ላይ ብቻ ተመርኩዞ የቆየውን የሰብአዊ ድጋፍ ስራዎች ለመከወን እንደዚህ አይነት ጥምረቶች መመስረታቸው ጥገኝነትን የሚቀንስና ከተረጂነት በመላቀቅ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የሚያግዝም ነው ብለዋል፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች እየቀነሰ የመጣውን የሰብአዊ ድጋፍ ተከትሎ ዜጎች ቋሚ እርዳታ ጠባቂና የሰዎችን እጅ ተመልካች እንዳይሆኑ ችግሩ ከተከሰተ በኋላ ብቻ ሳይሆን ቀድሞ በመዘጋጀት ያንን የሚቋቋም ማህበረሰብ መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ጥምረቱ በኢትዮጵያ የሚሰሩ ሀገር በቀል የልማት ድርጅቶች በጋራ ሆነው በተለይም ከዓለምአቀፍ ተቋማት ተረጂነት በመላቀቅ የጋራ መፍትሄ የሚፈልጉበት መሆኑን የነገሩን ደግሞ የቼንጅ ኮንሰርቲየም ሊቀመንበር የሆኑት ዶክተር አምበሱ ቶላ ናቸው፡፡
ድርጅቶቹ በኢትዮጲያ ውስጥ ያሉትን ችግሮች በመተባበር መፍትሄ መስጠትና ኢትዮጵያን ከድህነት ለማላቀቅ መንግስት በሚያደርገው ጥረት ተባባሪ በመሆን የልማት ስራዎችን መደገፍና ማበረታታት ላይ ይሰራል ብለዋል፡፡
ሀገር በቀል የልማት ድርጅቶቹ ከተለያዩ ዘርፎች የተሰባሰቡ ናቸው የሚሉት ዶክተር አምበሱ በስርዓተ ምግብ ተፈናቃዮችን ማቋቋም በአካል ጉዳተኞች ሴቶችና ሌሎችም መስኮች ላይ በተናጠል ሲሰሩ የነበረው ናቸው ብለዋል፡፡
በተለያዩ ውስጣዊ ችግሮች ምክንያት የሚደርስ መፈናቀል የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ የሚመጣ ድርቅ እንዲሁም ሌሎች ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮችን ለመቋቋም ሀገር በቀል የእርዳታ ተቋማትን ማጠናከርና ስራዎችን ወደዛ ማዞር ይገባል ተብሏል፡፡
ምህረት ስዩም
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
👇👇👇
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s











Comments