top of page

በኢትዮጵያ ማንም እየተነሳ ሐውልት እንዳያቆምና እንዳያፈርስ የሚከለክል የህግ ማዕቀፍ እንዲኖር ተጠየቀ፡፡

  • sheger1021fm
  • 6 hours ago
  • 3 min read

ጥቅምት 25 2018


በኢትዮጵያ ማንም እየተነሳ ሐውልት እንዳያቆም እና የቆሙትን ማንም ባሻው ሰዓት እንዳያፈርስ የሚከለክል የህግ ማዕቀፍ እንዲኖር ተጠየቀ፡፡


ይህ ጥያቄ የቀረበው ጥቅምት 22 ቀን 2018 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጻህፍት(ወመዘክር) ‘’ስለ አደባባይ ሐውልቶቻችን’’ በሚል ርዕስ በተሰናዳ ሥነ ጥባባዊ ወይይት ላይ ነው፡፡


የውይይቱን መነሻ ጹሁፍ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአለ ሥነ ጥበብ እና ዲዛይን ትምህርት ቤት ዲን ሠዓሊ አገኝሁ አዳነ የዘመን መልክ የሆኑ በሶስት ተከታታይ መንግስታት የተሰሩ የአደባባይ ሐውልቶችን የተመለከተ ዳሰሳ አቅርበዋል፡፡


ዳሰሳው የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባን መሰረት ተደርገው የተሰሩትን ሐውልቶች የተመለከተ ነው፡፡


የአደባባይ ሐውልቶች የዘመኑን መንፈስ የሚማርኩ፣ የመንግስታትን ዘመን ሃይል አሰላለፍ ሰለሚያሳዩ፣ የመንግስትን መዋቅራዊ ሁኔታ ስለሚጠቁሙ፣ የገነኑ ወይም ታሪካዊ ሁነቶችን ማለትም የድል፣ የሥርዓት ለውጥ፣ የአብዮት የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን ለማስታወስ፣ እንዲሁም የዘመኑን የሀገር ግንባታ ጥረቶችን የሚዘክሩ መሆናቸው ደግሞ የዘመኑን መልክ የሚያሳዩ እንደሚያስብላቸው ሠዓሊ አገኝሁ አዳነ ተናግረዋል፡፡

ree

በተጨማሪም የባህል እና የማንነት እመርታ በመቀመር አንድ ዘመን እንዲታወስበት የሚፈልገውን ቁምነገር የሚያገኝበት፣ የሚረዳበት ሌላው ደግሞ አንዱን አውሬ አድርጎ የሚስልበት አልያም የሚተችበት ከፍተኛው ማህበረ ባህላዊ ክዋኔ ስለሆኑ የአደባባይ ሐውልቶች፣ ኪነ ጥበቦች እና ኪነ ሕንፃዎች የዘመን መልክ ገላጭ ያሰኛቸዋል ተብሏል፡፡


ዘመኑን እና ዘመንኛውን ኢመዋቲ (immortal) ለማድረግም የአደባባይ ሐውልቶች ድርሻቸው እጅግ ከፍ ያለ ነው ተብሏል፡፡


ከአጼ ሚኒሊክ መታሰብያ ሃውልት ጀምሮ በቀዳማይ አፄ ኃይለ ስላሴ፣ በደርግ እና በኢህአዴግ ዘመን ስለተሰሩ የአደባባይ ሐውልቶች ገለፃ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የአለ ሥነ ጥበብ እና ዲዛይን ትምህርት ቤት ዲን ሠዓሊ አገኘሁ አዳነ በደርግ ጊዜ በከተማዋ ከቆሙ ሐውልቶች ይልቅ የፈረሱ ሐውልቶች እንደሚበልጡ ጠቁመዋል፡፡


እንደ ሠዓሊ አገኝሁ ማብራሪያ የንጉሠ ነገሥቱ፣ የመሳፍንቱ ፣ የመኳንንቱ እንዲሁም እነሱን ከፍ ከፍ የሚደርጉ ከሥርዓቱ ጋር የሚገኛኙ በተለያዩ ተቋማት፣ እና ጎዳናዎች የነበሩ ከጥቂቶች በስተቀር በሙሉ ፈርሰዋል፡፡


እንዳንዶቹ ጠፍተዋል ቀሪዎቹ ደግሞ ወደ ብሔራዊ ሙዚየም ተወስደዋል፡፡ ነገር ግን የተጣለው እንደሚበዛ ተነግሯል ፡፡


ደርግም በተራው ስልጣን ሲለቅ በቴክኒክ ረገድ ከፍ ያሉ፤ ቢኖሩ ደግሞ የማያጎሉ የሌኒን ጨምሮ በርካታ ሐውልቶች ፈርሰዋል ብለዋል፡፡


ከዓመታት በፊት የፈረሰው የሐረሩ የራስ መኮንን ሐውልት ታሪክ ብቻውን ብዙ የሚያነጋግር ብዙ ሊባልበት የሚገባ መሆኑን ያስረዱት ሰዓሊው ሐውልቱን የቀረፀው የታወቀ ቀራጺ ስለነበር ብቻ የዚህ ሰው ቅርስ ወይም ስራ በአገሪቱ አንድ ከፍል ውስጥ አለ ቢባል እንኳን ብዙ እናተርፍበት ነበር ሲሉ ተናግረዋል፡፡


ሐውልቶችን ማጥፋት እና ማፍረስ በኢትዮጵያ ብቻ የተሰራ ጥፋት አይደለም በሌሎች አህጉራት ባሉ አገሮችም ተመሳሳይ ጥፋቶች መፈጸማቸውን የሚስታውሱት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአለ ሥነ ጥበብ እና ዲዛይን ትምህርት ቤት ዲን ይህ ግን ለእኛ አያዋጣም ምክንያቱ ረጅም የሥነ ጥበብ ታሪክ ቢኖረንም እንደ ትልቅነታችን እንደ አገሩም ስፋት የኪነ ጥበብ ስራዎቻችን ብዙ አይደሉም ብለዋል፡፡


ሰዓሊው “የኪነ ቅርስ ድርቅ የመታው ሀገር ነው ያለን’’ ሲሉም አብራርተዋል፡፡


ሰዓሊ አገኝሁ አዳነ ‘’አንድን ቅርስ ማጥፋት የታሪክ ፍጻሜ ሳይሆን የመዘንጋት ጅማሮ ነው” የሚልን ብሂል አስታውሰው መሰል ስህተቶች መደገም የለባቸውም ሲሉ ተናግረዋል፡፡


አሳዬ ንጉሴ የተባሉ ተሳታፊ በበኩላቸው የፈረሰውን የራስ መኮንን ሐውልት ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች ያሉ ሐውልቶች መጎብኘታቸውን አስታውሰው ማን አፈርሰው? ለምን ፈረሰ? የሚለው ዝም ተብሎ መታለፍ ያለበት ነገር አይመስለኝም ይላሉ።


አቶ አሳዬ ይህን ያነሱበትን ምክንያት ሲያስረዱ ደግሞ በእኛ ዘመንም ኮንሰርት ጭምሮ የተለያዩ አለም አቀፍ ኩነቶች ተደርገው የቦብ ማርሌይ ሐውልት ገርጂ ኢምፔሪያል አካባቢ ቆሞ እንደነበር አስታውሰው አሁን ግን የት እንዳለ አይታወቅም ከእነዚህ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ነገሮች ጥልቅ ጥናት ይፈልጋሉ ብለዋል።


የሚመለከተው አካል ምን ያህል ሃላፊነቱን እየተወጣ እንደሆነም አይታወቅም፤ ያሉት ተሳታፊው መሰል ስህተቶችም እንዳይደገሙም መመሪያ ማዘጋጀት ቢቻል ሲሉ ሃሳባቸውን ተሰጥተዋል።

ree

የሕግ ጉዳዮች ጣናት ባለሞያ ሃይማኖት ደበበ ጉዳዩ ብዙ ጊዜ ለውይይት እንደማይቀርብ ጠቁመዋል፡፡


ጉዳዩ ለውይይት መቅረቡ አስፈላጊ መሆኑን የጠቆሙት ተሳታፊዋ አንዳንዴ ሐውልቶቻችን ዝም በሎ በሞቅታ ከምንም ጋር ሳይገናኙ የሚሰሩ አሉ ይህ እንዴት ነው የሚታው? ሲሉ ጠይቀዋል።


የሕግ ጉዳዮች ጥናት ባለሙያዋ ሃይማኖት ደበበ ሐውልቶች የጭቅጭቅ መነሻ መሆናቸውን ተናግረው የጋራ ቤት እንገነባለን ብለን ስለምናስብ መቼ ነው የምንስማማበትን ነገር የምንሰራው? ምክንያቱም ለእኔ ጅግና የሆነ ለሌላ ሰው ጀግና ላይሆን ይችላል ሲሉ አክለዋል።


ስለዚህ ይህን የምንቆጣጠርበት የህግ ማዕቀፍ አያስፈልገውም ወይ? ለምሳሌ በፍረንጆቹ 2020 ላይ በአሜሪካ ሐውልቶች ላይ ልክ እንደ ኢትዮጵያ መሰል ጭቅጭቅ ሲነሳ እንደነበር እና ባለፈው ነሃሴ (August) ወር ላይ ፕሬዘዳንት ትራንፕ ምልሽ እንደሰጡበት አስታውሰዋል፡፡


በተመሳሳይ በሌሎች አገራትም በዚህ ጉዳይ ላይ ህዝባዊ ወይይቶች ይደረጋሉ ያሉት ሃይማኖት ደበበ እኛ አገር ይሄ መቼ ነው የሚደረገው? ሲሉ ጠይቀዋል።


ጉዳዩን በተመለከተ የህግ ማዕቀፍ ያስፈልጋል አለበለዚያ ልንግባባ አንችልም ብለዋል።


ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ ሣዓሊ እሸቱ ጡሩነህ በበኩላቸው የህግ ማዕቀፍ ይኑረው በሚል የቀረበው ሃሳብ እና ጥያቄ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

ree

የህግ ማዕቀፉ ለኢትዮጵያ በብዙ መልክ እንደሚጠቅም የተናገሩት ሣዓሊ እሸቱ ህዝብ ማይወደውም ህዝብ የሚውደውም ሊኖር ይችላል፤ ነገር ግን ህዝብን ከቁጣው፣ ከደስታው ጋራ ሊያነጻጽር የሚችል ማለትም ለህግ ተቆጣጣሪው አካል ይሰጣል ብለዋል።


በዚሀም አፍርሶ እንዴት እንደሚተካ ፣ ወዴት እንደሚወሰድ ሥርዓት ካለ አሁንም ላሉትም፣ ወደፊትም ለሚሰሩትም ዋስትና ይሆናል ካልሆነ ግን ለሁሉም ዋስትና የለም ሲሉ አብራርተዋል።


ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡት አገኘሁ አዳነ የህግ ማዕቀፍ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል።


ማንም እንደፈለገ የፈለገውን ቀርጽ የሚያቆምበት ሥርዓት አይኖርም በሌላው አለም ሥርዓት እና የህግ ማዕቀፍ አለ ለዚህ በመነጋገር እና በመተማመን የሆነ ነገር ማድረግ ይኖርብናል ብለዋል።


አንድ ሐውልት በተለያየ ምክንያት ማህበረሰብን ሊያስቀይም የሚችል ምልክት አለው ተብሎ ሲታመን ለማንሳት የራሱ አሰራርና ሂደት ሊኖረው ይገባል ተብሏል፡፡


በተመሳሳይ ሐውልት ሲቆምም የህግ ማዕቀፍ ያስፈልጋል ተብሏል፡፡


ህጉ ካለ በድንገት የሚቆሙ ሐውልቶች አይኖሩም የሚቆሙ ሐውልቶችም ሀገር የሚመጥኑ ይሆናሉ ሲሉም አስረድተዋል።


ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ….


ያሬድ እንዳሻው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

👇👇👇


Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page