top of page

ቁጥሩ ከግማሽ በላይ ቀንሶ እየተመናመነ ያለው ዋልያ አሁንም ማገገም አላሳየም ተባለ

  • sheger1021fm
  • 8 minutes ago
  • 1 min read

ህዳር 3 2018


በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የሚገኘውና ቁጥሩ ከግማሽ በላይ ቀንሶ እየተመናመነ ያለው ዋልያ አሁንም ማገገም አላሳየም ተባለ።


ከቅርብ ወራት በፊት የተደረገ ድጋሚ ቆጠራ በፓርኩ የሚገኙ ዋልያዎች ብዛት አሁንም 306 መሆኑን አሳይቷል ተብሏል።


ለዋልያ ቁጥር መመናመን አንዱ ምክንያት የሰሜኑ ጦርነት ነበር ተብሏል፡፡

በኢትዮጵያ ብቻ ከሚገኙ ብርቅዬ የዱር እንስሳት አንዱ የሆነው ዋልያ ቁጥሩ ከግማሽ በላይ ቀንሶ እየተመናመነ እንደሚገኝ ከዚህ ቀደም መነገሩ ይታወሳል፡፡

ree

ከወራት በፊት በተደረገ የድጋሚ ቆጠራ በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ያሉ ዋልያዎች ብዛት አሁንም 306 እንደሆነ መረጋገጡን፤ በባለስልጣኑ የብሄራዊ ፓርኮች አስተዳደር መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አዳነ ፀጋዬ ነግረውናል።


የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ባለበት አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች የኢኮኖሚ መሰረታቸውን በቱሪዝም ላይ ያደረጉ እና፤ ስለፓርክም ግንዛቤ ያላቸው በመሆናቸው የዋልያ አደን አልነበረም ያሉን ዶክተር አዳነ ፤ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የነበረውን ጦርነት ተከትሎ ግን ሁኔታዎች መቀየራቸውን ተናግረዋል።


ዋልያ በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ይገኛል ቢባልም መኖሪያው ከፓርኩም ውስን በሆነ አካባቢ ብቻ ነው የሚሉት ዶክተር አዳነ ፤

በዚህ መኖሪያቸው የታየው የሰዎች እንቅስቃሴም ቁጥራቸው እንዲመናመን ያደረገ ተጨማሪ ምክንያት መሆኑን ነግረውናል።


በፓርኩ ያለው የዋልያ ቁጥር እንዲጨምር ስትራቴጂ ማዘጋጀትን ጨምሮ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙም ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።


መኖሪያ አካባቢያቸውን ከሰዎች እንቅስቃሴ ነጻ ማድረግ እና ህገ ወጥ አደኑን መቆጣጠር ከተቻለ የዋልያ ቁጥር አጠር ባለ ጊዜ መልሶ ሊያገግም ይችላል ወይ ያልናቸው ዶክተር አዳነ ተከታዩን መልሰዋል።


የዋልያ መገኛ የሆነው የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የበርካታ ተፋሰሶች መነሻ እና ከቱሪዝም አኳያም ጥሩ ደረጃ ላይ የደረሰ እንደሆነ ተነግሯል።


የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከዋልያ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኙ እንደ ቀይ ቀበሮ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ፣ የምኒልክ ድኩላና የመሳስሉ ብርቅዬ እንስሳት መገኛ ነው።


ንጋቱ ረጋሳ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

👇👇👇


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page