ሰኔ 19 2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች
- sheger1021fm
- Jun 26
- 2 min read
ኬንያን ትናንት ሲንጣት የዋለ የፀረ መንግስት የተቃውሞ ሰልፍ ባስከተለው ግጭት በጥቂቱ የ8 ሰዎች ሕይወት ተቀጠፈ ተባለ፡፡
በመዲናይቱ ናይሮቢ እና በተለያዩ የኬኒያ ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች እንደተደረጉ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
በብዙ ቦታዎች የተቃውሞ ሰልፈኞቹ ከፖሊሶች ጋር ክፉኛ መጋጨታቸው ተሰምቷል፡፡
በዚህም በጥቂቱ 8 የተቃውሞ ሰልፈኞች መገደላቸውን የህክምና እና የህግ ባለሙያዎች ማህበራት ጥምረት እወቁልኝ ብሏል፡፡

በ400 ሰዎች ላይ ደግሞ የተለያየ ደረጃ አካላዊ ጉዳት መድረሱ ተጠቅሷል፡፡
ሰልፉ የተደረገው አምና ከ60 ያላነሱ ሰዎች ያለቁበትን የተቃውሞ ሰልፍ 1ኛ አመት ምክንያት በማድረግ ነው ተብሏል፡፡
ሰልፉን በቀጥታ ሲዘግቡ የነበሩ የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ስርጭት እንዲያቋርጡ መደረጋቸው ተጠቅሷል፡፡
ሰልፈኞቹ ፕሬዘዳንት ዊሊያም ሩቶ ስልጣን እንዲለቁ መጠየቃቸው ተሰምቷል፡፡
ፕሬዘዳንቱ ደግሞ ያለችን አንዲት አገር ነች ለምን እናፈራርሳታለን ሲሉ ተቃውሞው እንዲያበቃ ተማፅነዋል ተብሏል፡፡
የአሜሪካ ማዕከላዊ የስለላ ድርጅት /CIA/ የበላይ ጆን ራትክሊፍ የኢራን የኒኩሊየር ተቋማት በአሜሪካ ድብደባ እጅግ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል አሉ፡፡
ቀደም ሲል የአሜሪካ መከላከያ መስሪያ ቤት(ፔንታገን) የወታደራዊ ደህንነት የድብደባ ምዘና ቀዳሚ ሪፖርት አፈትልኮ ወጥቷል መባሉ ጉዳዩን አነጋጋሪ ማድረጉን ቢቢሲ ፅፏል፡፡
ከመከላከያ መስሪያ ቤቱ /ፔንታገን/ አፈተለከ የተባለው መረጃ ድብደባው የኢራንን መርሐ ግብር ቢያዘገየው ለወራት ሊሆን እንደሚችል የሚጠቁም ነበር፡፡
የ CIAው ዋና ዳይሬክተር ግን ድብደባው የኢራንን የኒኩሊር መርሐ ግብር ለብዙ አመታት ወደ ኋላ ይጎትተዋል ማለታቸው ተጠቅሷል፡፡
አሜሪካ በእስራኤል ተደራቢነት በፈፀመችው ድብደባ የኢራንን የፎርዶ ፣ የኢስፋሐን እና የናታንዝን የኒኩሊየር ተቋማት መምታቷን መረጃው አስታውሷል፡፡
በ12ቱ ቀናት ከባድ ግጭት ኢራን እና እስራኤል በየፊናቸው አሸንፈናል እያሉ ነው፡፡
ከዚህ አለም በሞት የተለዩት የዛምቢያ የቀድሞ ፕሬዘዳንት ኤድጋር ሉንጉ የቀብር ሥነ ሥርዓት በመጨረሻው ሰዓት ተስተጓጎለ፡፡
የሉንጉን ቀብር በጎረቤት ደቡብ አፍሪካ ለማከናወን ዝግጅቱ ተጠናቆ እንደነበር ቢቢሲ ፅፏል፡፡
በኤድጋር ሉንጉ የሐዘን እና የቀብር ሥነ ሥርዓት ጉዳይ የቀድሞው ፕሬዘዳንት ቤተሰብ ከመንግስት ጋር ሲወዛገብ መክረሙ ተጠቅሷል፡፡
የዛምቢያ መንግስት የሉንጉ ቀብር በደቡብ አፍሪካ እንዳይከናወን ለፕሪቶሪያ ፍርድ ቤት ባቀረበው አቤቱታ የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው መስተጓጎሉ ታውቋል፡፡
የአሁኑ የዛምቢያ ፕሬዘዳንት ሐይኪይንዴ ሒቺሌማ ቀዳሚያቸው የአገር መሪ የነበሩ በመሆኑ ቀብራቸው በዛምቢያ መፈፀም ይኖርበታል እያሉ ነው፡፡
የቀድሞው ፕሬዘዳንት ቤተሰቦች ደግሞ ሉንጉ በሕይወት ሳሉ ሒቺሌማ በቀብሬ ላይ እንዳይገኝ የሚል ኑዛዜ በመተዋቸው ይሄን ፍላጎታቸው ለመሙላት ሕይወታቸው ባለፈበት በደቡብ አፍሪካ እንዲቀበሩ መወሰናቸው ታውቋል፡፡
የሩሲያ መንግስት ኢራን ከአለም አቀፉ የአቶሚክ ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ /IAEA/ የነበራትን ትብበር ለማቋረጥ እንድትወስን በእስራኤል እና በአሜሪካ የተፈፀመባት ድብደባ ገፊው ምክንያት ነው አለ፡፡
የክሬምሊኑ ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ድብደባው ኢራን ከተቆጣጣሪ ኤጀንሲው ጋር ትብብሯን እንድታቋርጥ ቀጥተኛው ምክንያት ነው ማለታቸውን አናዶሉ ፅፏል፡፡
የተቆጣጣሪው አካል አቋም ኢራን እንድትመታ ቀጥተኛም ባይሆን በተዘዋዋሪ አስተዋጽኦ ማድረጉን ፔስኮቭ ተናግረዋል፡፡
በድብደባው በኢራን የኒኩሊር መርሐ ግብር ላይ ስለ ደረሰው ጉዳት እቅጩን ለማወቅ ጊዜው ገና ነው ብለዋል የክሬምሊኑ ቃል አቀባይ፡፡
የእስራኤል እና የአሜሪካ መንግስታት በየፊናቸው በኢራን የኒኩሊየር መርሐ ግብር ላይ እጅግ የገዘፈ ጉዳት አድርሰናል ባዮች ናቸው፡፡
ኢራን ደግሞ በድብደባው በኒኩሊየር መርሐ ግብሯ ላይ የደረሰውን ጉዳት እያቃለለችው ነው፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il












Comments