ሰኔ 13 2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች
- sheger1021fm
- 3 hours ago
- 2 min read
እስራኤል እና ኢራን አንዷ በሌላዋ ላይ ከባድ ጥቃት እያደረሱ ነው፡፡
እስራኤል በኢራኗ ርዕሰ ከተማ ቴሕራን እና ሌሎችም ስፍራዎች ያነጣጠረ ከባድ ድብደባ እየፈፀመች መሆኑን አልጀዚራ ፅፏል፡፡
ኢራንም ትናንት በደቡባዊ እስራኤል በፈፀመችው ከባድ የሚሳየል ድብደባ የሶሮካን ሆስፒታል መምታቷ የእስራኤል ሹሞችን በእጅጉ አንጨርጭሯቸዋል 71 ሰዎች ቆስለዋል ተብሏል፡፡
የኢራን ሹሞች ዋነኛ ዒላማችን በሆስፒታሉ አቅራቢያ ያለ ወታደራዊ ተቋም ነው ማለታቸውን ቢቢሲ ፅፏል፡፡
ዘግየት ብሎ ደግሞ የኢራን ሹሞች መርዘኛ ፕሮፓጋንዳ እየረጨ ነው ያሉትን የእስራኤሉ ቻናል 14 ቴሌቪዝን ጣቢያ ለመምታት በአቅራቢያ እና ዙሪያ ገባው ያሉ ነዋሪዎች ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቃቸው ተሰምቷል፡፡
ሰሞኑን የእስራኤል ጦር በቴሕራን በመንግስታዊው ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ድብደባ መፈፀሙ ይታወቃል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ብርጋዲየር ጄኔራል ማጂድ ካዴሚ አብዮታዊ ዘብ የተሰኘው የኢራን የጦር ክፍል የወታደራዊ ደህንነት የበላይ ተደርገው መሾማቸውን የፃፈው ደግሞ አናደሉ ነው፡፡
በእስራኤሉ ቴል አቪቭ ከተማ በኖርዌይ ኤምባሲ አቅራቢያ ከፍተኛ ፍንዳታ እንደነበር ኤምባሲው እወቁልኝ ማለቱ በመረጃው ተጠቅሷል፡፡
አሜሪካ በእስራኤል ተደራቢነት በኢራን ላይ የጦር እርምጃ ከመውሰድ እንድትቆጠብ ሩሲያ በብርቱ አስጠነቀቀቻት፡፡
የሩሲያ ማስጠንቀቂያ የተሰማው በውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይዋ ማሪያ ዛኻሮቫ አማካይነት እንደሆነ AFP ፅፏል፡፡
ማሪያ ዛኻሮቫ አሜሪካ በኢራን ላይ የጦር እርምጃ ወደመውሰድ ካመራች በጣም ያልተጠበቀ አሉታዊ ውጤት ሊያስከትል ይችላል ብለዋል፡፡

ቀደም ሲል የሩሲያው ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የቻይናው አቻቸው ሺ ጂን ፒንግ እስራኤል በኢራን ላይ የምትፈፅመውን የጦር ጥቃት ማውገዛቸው በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
የሁለቱ አገሮች ግጭት በዲፕሎማሲያዊ መላ ማብቂያ እንዲበጅላት ጠይቀዋል ተብሏል፡፡
አሜሪካ በእስራኤል ተደራቢነት ኢራንን ለመምታት እየተዘጋጀት ነው የሚለው ግምት ማየሉን መረጃው አስታውሷል፡፡
ሩሲያ አሜሪካን ያስጠነቀቀቻት በኢራን የኒኩሊየር ተቋማት ላይ በሚፈፀም ከባድ ድብደባ አደገኛ እና መራዥ ጨረር ሊያፈተልክ ይችላል በሚል ምክንያት መሆኑ ታውቋል፡፡
ዩክሬይን በእስራኤል እና በኢራን መካከል የተከሰተው ግጭት የእኔን ጉዳይ እንዲዘነጋ ያደርግብናል ስትል ስጋት እንደገባት ተሰማ፡፡
የዩክሬይን ሹሞች ሩሲያ በባህረ ሰላጤው ጦርነት ሽፋን አስቀድማ ያበረታችብንን ድብደባ ልታከፋብን ትችላለች ሲሉ ስጋት ገብቷቸዋል መባሉን AFP ፅፏል፡፡
በዚያ ላይ በባሕረ ሰላጤው ቀውስ የተነሳ የነዳጅ ዋጋ መጨመሩ የሩሲያን የጦር ማከናወኛ ገቢ ሊያዳብርላት ይችላል የሚለው ጉዳይ የዩክሬይን ሹሞች ሌላኛው ስጋት ነው ተብሏል፡፡
በተረፈ የዩክሬይን ሹሞች እስራኤል ኢራንን መምታቷን እሰየው ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
ዩክሬይን ኢራንን ለሩሲያ ሚሳየል እና ድሮኖችን ታቀብላለች በሚል ስትከሳት መቆየቷን መረጃው አስታውሷል፡፡
የባሕረ ሰላጤው ጦርነት የኔ ጉዳይ እንዲዘነጋ ሊያደርገው ይችላል የሚል ስጋት እንደገባት ተጠቅሷል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በእስራኤል ተባባሪነት ኢራንን በጦር ለመምታት ውሳኔ ላይ ለመድረስ የሁለት ሳምንታት ጊዜ ያሻኛል ማለታቸውን የዋይት ሐውሷ ቃል አቀባይ ተናገሩ፡፡
ትራምፕ ኢራንን ለመምታት ቁርጥ ካለ ውሳኔ ላይ ያልደረሱት ከኢራን ጋር ይደረጋል ለተባለ ድርድር እድል ለመስጠት ነው መባሉን አልጀዚራ ፅፏል፡፡
አንደ የአሜሪካ የቀድሞ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ትራምፕ ለውሳኔ ያልተጣደፉት ጉዳዩ በሪፖብሊካውያን ደጋፊዎቻቸውም ዘንድ ከፍተኛ ክፍፍል በመፍጠሩ ምክንያት ነው ብለዋል፡፡
የአሜሪካ ትቅደም አቀንቃኝ የሆኑ ሪፖብሊካውያን እዚያ ማዶ በሚደረግ ጦርነት እኛ ምን አገባን በሚል ፕሬዘዳንቱን እንደጠሯቸው አንስተዋል የቀድሞው የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ፡፡
በሌላ በኩል አሜሪካ ኢራንን ለመምታት ከእስራኤል ጎን መሰለፍ አለባት ባዮች እንዳሉም ጠቁመዋል፡፡
የእስራኤል ሹሞች ግን የአሜሪካን ተደራቢነት ቢሹትም ያለ አሜሪካ ተሳትፎም ቢሆን የኢራንን ተልዕኳችንን ለማጠናቀቅ ቢጠይቀን የሁለት ሶስት ሳምንታት ጊዜ ነው እያሉ ነው፡፡
የኢራን ሹሞችም አሜሪካ በእስራኤል ተደራቢነት ወደ ጦርነቱ እንዳትገባ በብርቱ አስጠንቅቀዋል፡፡
ይሄ የአሜሪካ ጦርነት አይደለም ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
留言