top of page

ሚያዝያ 21፣2016 - የባህር ማዶ ወሬዎች


በተለያዩ የአለም ክፍሎች የተለያዩ ቀውሶች መነባበር የሰብአዊ የምግብ እርዳታ አቅርቦቱን በእጅጉ ፈታኝ እያደረገው ነው ተባለ፡፡


በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት በመካከለኛው ምስራቅ የአለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) የበላይዋ ኮርኔ ፍሌሸር እንደሆኑ አረብ ኒውስ ፅፏል፡፡


የምግብ እጦት ቀውሱ አድማሱ ሲሰፋ በአንፃሩ የለጋሾች እርዳታ መቀነሱ ችግሩን እያባባሰው ነው ብለዋል፡፡

በዚህ የተነሳም ድርጅታቸው የእርዳታ እህል እና ምግብ አቅርቦቱን ለመቀነስ እንደተገደደ ተናግረዋል፡፡


በዚያ ላይ በተለያዩ ሀገሮች የምግብ ዋጋ አልቀመስ እያለ መምጣት ሌላኛው የችግር አባባሽ ክስተት እንደሆነ አንስተዋል፡፡


ነገሩ ፈታኝም ከባድም ነው ማለታቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡



የፍልስጤም አስተዳደር ፕሬዘዳንት ማሐሙድ አባስ እስራኤል በራፋ ያሰበችውን መጠነ ሰፊ የጦር ዘመቻን አሜሪካ እንድታስቆመው ተማፀኑ፡፡


የእስራኤል መንግሰት ማንም ምንም ቢል የራፋ ዘመቻዬ አይቀሬ ነው በሚል ሲዝት መሰንበቱን አልጀዚራ ፅፏል፡፡


ራፋ በጋዛ ሰርጥ ደቡባዊ ጠርዝ በግብፁ የሲናይ ልሳነ ምድር አዋሳኝ የምትገኝ ከተማ ነች፡፡


ከከተማዋ ነዋሪዎች በተጨማሪ በእስራኤል ዘመቻ ከተለያዩ የጋዛ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ከሚሊዮን የማያንሱ ፍልስጤማውያንም የተጠለሉባት እንደሆነች ይነገራል፡፡


እስራኤል መጠነ ሰፊውን ዘመቻ የምታካሂድ ከሆነ ሰብአዊ ቀውሱን በእጅጉ እንደሚያባብሰው ተሰግቷል፡፡


እስራኤል በራፋ ከወዲሁ የአየር ድብደባ እየፈፀመች መሆኑ ይነገራል፡፡



የዩክሬይኑ የጦር አዛዥ ጄኔራል አሌክሳንደር ሳርስኪዬ በምስራቃዊ የአገሪቱ ክፍል ወታደሮቻቸው እያፈገፈጉ መሆኑን ተናገሩ፡፡


ሳርስኪዬ የሰራዊታቸውን እግር መንቀል ስልታዊ ማፈግፈግ ሲሉ መጥራታቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡


የዩክሬይን ሰራዊት አዛዥ ሰሞኑን የሩሲያ ጦር ማጥቃት በእጅጉ እንደበረታባቸው አልሸሸጉም፡፡


እንደሚባለው የሩሲያ ጦር በምስራቃዊ ዩክሬይን ወደ ቀጣይ ድል መረማመድ የሚያስችሉትን የጦር ውጤቶች እያስመዘገበ ነው፡፡


የሩሲያ ጦር ከአቭዲቭካ ከተማ በስተሰሜን በ15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝን ስፍራ መቆጣጠሩን የመከላከያ ሹሞች የተናገሩት ሰሞኑን ነው፡፡


የዩክሬይን የጦር ሹሞች የወታደሮች እና የጦር መሳሪያ እጥረት እንደገጠማቸው በተደጋጋሚ እየተናገሩ ነው፡፡

ጦርነቱ ከ 2 አመታት በላይ ሆኖታል፡፡



በኮንጎ ኪንሻሣ በተልዕኮ ላይ የቆየው የተባበሩት መንግስታት ሰላም አስከባሪ በምስራቃዊ የአገሪቱ ክፍል የሚገኘውን ዋና ጦር ሰፈሩን ዘጋው፡፡


የጦር ሰፈሩ መዘጋት ሙንስኮ በሚል ምህፃር የሚታወቀው ሰላም አስከባሪው ሀይል ከዚያች አገር ጠቅልሎ የመውጫ እቅድ አካል እንደሆነ አልጀዚራ ፅፏል፡፡


የተዘጋው የሙንስኮ ዋና ጦር ሰፈር በምስራቃዊ ኮንጎ ቡካቩ ከተማ የሚገኝ ነው ተብሏል፡፡


ሰላም አስከባሪው ከአማፂያን አላስጣለንም በሚል ህዝባዊ ተቃውሞ ሲቀርብበት መቆየቱን ዘገባው አስታውሷል፡፡


ከኮንጎ ኪንሻሣ የሚወጣውም በአገሪቱ መንግስት ጥያቄ መሰረት ነው፡፡


ከኮንጎ የሚወጣው ሙንስኮ በዚያ ከ20 አመታት በላይ መቆየቱን ዘገባው አስታውሷል፡፡


የኔነህ ከበደ



የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


Telegram: @ShegerFMRadio102_1




bottom of page