top of page

ሚያዝያ 15፣2016 - አዲሱ የካላዛር ህክምና ወደ ምዕራፍ ሁለት የክሊኒካል ሙከራ መሸጋገሩ ተሰማ

ካላዛር ከወባ ቀጥሎ በዓለም ላይ በጥገኛ ተህዋሲያን የሚተላለፍ ገዳዩ በሽታ ነው፡፡


በሽታው ትኩሳት፣ የክብደት መቀነስ፣ ከልክ ያለፈ የጣፊያና የጉበት እድገት ያስከትላል፣ በጊዜው ካልታከመም ለሞት ሊዳርግም ይችላል፡፡


ፈውስ ትኩረት ለተነፈጉ በሽታዎች ኢኒሺዬቲቭ ወይንም ዲ ኤን ዲ የጤና ምርምር የተባለ ተቋም እና አጋሮቹ ለዚህ በሽታ የሚያደርጉት የመድሃኒት ፍለጋ ምእራፍ ሁለት የክሊኒካል ሙከራ ደረጃ መሸጋገሩን ተናግሯል፡፡


ወደ ምእራፍ ሁለት የክሊኒካል ሙከራ መሸጋገሩ የተነገረው መድሃኒቱ ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ፣ አስተማማኝ፣ ለአጠቃቀም ቀላል እና ለህሙማን ምቹ የሆነ በአፍ የሚወሰድ ነው ተብሏል፡፡

የካላዛር መድሃኒት ለማስገኘት የሚያካሂዱት ምርምር አዲሱ የካላዛር ህክምና በእጅጉ ትኩረት የተነፈገውንና ለማከምም አስቸጋሪ የሆነውን የካላዛር በሽታ ለማዳን በሚደረገው ርብርብ ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ያግዛል ተብሎለታል፡፡

በአፍሪካ አሁን እየተሰጠ የሚገኘው የካላዛር ህክምና በሆስፒታል ውስጥ በየቀኑ ለ17 ቀናት የሚወሰድ ከፍተኛ ህመም የሚፈጥር ክትባት ሲሆን ልብን፣ጉበትን እና ቆሽትን በመጉዳት ለህይወት አስጊ የሆኑ የጎንዮሽ ጉዳቶችን ሊያስከትል ይችላል።


በአንፃሩ በኢትዮጵያ በምርምር ላይ የሚገኘው አዲሱየ“LXE408”በአፍ የሚወሰድ መድሀኒት አሁን ከሚሰጠው ህክምና የበለጠ ፈዋሽና አስተማማኝ እንደሚሆን ይጠበቃል ተብሏል።


“ኢትዮጵያ እንደ አንድ ካላዛር የተንሰራፋበት አገር፣አዳዲሶቹ ኬሚካላዊ ምርምሮች ወደሚካዱበት ምእራፍ ሁለት ክሊኒካዊ ሙከራ መግባቷ ትልቅ እምርታ ነው ሲሉ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የካላዛር በሽታ ጥናትና ህክምና ማዕከል ውስጥ በሚካሄደው በዚህ ክሊኒካል ሙከራ ተባባሪ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር እሌኒ አየለ አስረድተዋል፡፡


“አሁን ላይ በኢትዮጵያ ያሉት የካላዛር ህክምና አማራጮች ከፍተኛ የሆነ ውስንነት ያለባቸው፣ ጎጂ ክትባትን ግዴታ የሚያደርጉ፣ እጅግ ቀዝቃዛ የህክምና ቁሳቁሶች ጥቅም ላይ የሚውሉባቸው እንዲሁም ህሙማን አገልግሎቶቹን ፍለጋ የረጅም ርቀት ጉዞ የሚጠይቁ እና ለረጅም ጊዜም ሆስፒታል ውስጥ ተኝተው የሚታከሙባቸው ናቸው" ሲሉም ተመራማሪዋ ጠቅሰዋል፡፡

በምርምሩ ከሰመረ ላይ ህክምናው ፈዋሽ፣ የጎንዮሽ ጉዳቱ አነስተኛ የሆነና ህሙማን በመኖሪያ ቤታቸው ፣አቅራቢያ በሚገኙ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ተቋማት ማግኘት ይትላሉ ሲሉ ተመራማሪዋ አስረድተዋል፡፡


ከምንም በላይ በሽታውን እስከወዲያኛው ለማስወገድ የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ ያግዛል ተብሏል፡፡


አዲሱ ህክምና በኢትዮጵያ የመድሃኒትሙከራ መስፈርት መሰረት የሚካሄድ ሲሆን በየቀኑ የሶዲየም ስቲቦግሉኮኔት እና ፓሮሞማይሲን ድብልቅ መርፌዎች ለ17 ቀናት ይሰጣል።


ለዚህም ይረዳ ዘንድ ከ18 እስከ 44 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ 52 ፈቃደኛ ጎልማሶች በጥናቱ ይሳተፋሉ ተብሏል።


ተመሳሳይ የሁለተኛው ምእራፍ የ”LXE408”ክሊኒካዊ ሙከራ በህንድ አገር እየተከናወነ ሲሆን በምስራቅ አፍሪካና ደቡብ እስያ የሚገኙ ህሙማን ለዚህ ምርምር የተለያየ ምላሽ እንደሚያሳዩ ይጠበቃል ሲል የምርምር ተቋሙ ለሸደር በላከው መግለጫ ላይ ጠቅሷል፡፡


እተደረገ ያለው የካላዛር መድሃኒት ምርምር ለታካሚ ተስማሚ ፣ ለሁሉም ሰው ተደራሽ የሆኑ ውጤታማ መድሃኒቶችን ለማስገኘት አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተስፋ እናደርጋለን ሲሉ በዲኤንዲ የካላዛር ፕሮግራም ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ፋቢያና አልቬዝ ተናግረዋል፡፡


የህክምና ግኝቱ እና ህክምናውን በክሊኒካዊ ምርምር በማዘመን የሚደረገውን ጥናት በብሪታንያው ግብረሰናይ ድርጅት ዌልካም የገንዘብ ድጋፍ የተካሄደ ነው መሆኑ ተሰምቷል፡፡


በኢትዮጵያ የተካሄደው ክሊኒካዊ ሙከራ ደግሞ የገንዘብ ድጋፉን ያገኘው ከአውሮፓና በማደግ ላይ ያሉ አገራት ክሊኒካዊ ሙከራዎች ጥምረት (EDCPT) ነው።

ካላዛር በአሸዋ ዝንብ ንክሻ የሚተላለፍ ሲሆን በምስራቅ አፍሪካ፣ ደቡብ እስያ እና ደቡብ አሜሪካ በሚገኙ 80 አገራት ውስጥ ተንሰራፍቷል፡፡


አብዛኞቹ ህሙማንም በምስራቅ አፍሪካ ይገኛሉ ተብሏል።


የአየር ንብረት ለውጥ የካላዛር በሽታን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት በማወክ በሽታው እስካሁን ወዳልተዳረሰባቸው ቦታዎች እንዲስፋፋ ሊያደርግ ይችላል፡፡


በአለም ላይ በየአመቱ ከ50,000 እስከ 90,000 የሚደርሱ ሰዎች በካላዛር የሚያዙ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ገሚሱ እድሜያቸው ከ15 አመት በታች የሆኑ ህጻናት ናቸው፡፡


ንጋቱ ሙሉ



የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


Telegram: @ShegerFMRadio102_1




bottom of page