top of page

መጋቢት 23፣2016  - የባህር ማዶ ወሬዎች

 

በእስራኤል በጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ የሚመራው መንግስት ህዝባዊ ተቃውሞ በርትቶበታል ተባለ፡፡

 

ትናንት በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ እስራኤላዊያን በኢየሩሳሌም ታላቅ የተቃውሞ ሰልፍ ማድረጋቸውን ቢቢሲ ፅፏል፡፡

 

የተቃውሞ ሰልፉ የተደረገው የጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁን የጦር ወቅት አመራር በመቃወም ነው፡፡

 

የእስራኤል ጦር የጋዛ ዘመቻውን ከጀመረ መንፈቅ ሊሆነው ነው፡፡

 

ሰልፈኞቹ በአገሪቱ አጣዳፊ ምርጫ ተደርጎ ኔታንያሁ በሌላ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊተኩ ይገባል ብለዋል፡፡

 

በሐማስ ተይዘው የሚገኙ ከ130 የማያንሱ ታጋቾች እንዲለቀቁ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርግ መጠየቃቸውም ተሰምቷል፡፡



 

በደቡብ አፍሪካ MK የተሰኘው አዲስ የፖለቲካ ማህበር የቀድሞው ፕሬዘዳንት ጃኮብ ዙማ በግንቦቱ ምርጫ እንዲወዳደሩ የማልፈነቅለው ድንጋይ የለም አለ፡፡

 

የአገሪቱ ምርጫ አከናዋኝ መስሪያ ቤት ባለፈው ሳምንት ዙማ በምርጫው መፎካከር አይችሉም ማለቱን ዘ ኢስት አፍሪካን ፅፏል፡፡

 

በአገሪቱ የአመት እና ከዚያም በላይ እስር የተፈረደበት ግለሰብ በምርጫ መፎካከር እንደማይችል ዘገባው አስታውሷል፡፡

 

ዙማ የእስር ጊዜያቸውን ሳያጠናቅቁ ቢወጡም በችሎት መድፈር የ15 ወራት እስር ተፈርዶባቸው እንደነበር ለትውስታ ተጠቅሷል፡፡

 

የ MK የፖለቲካ ማህበር መጠሪያም እያወዛገበ ነው፡፡

 

MK ደቡብ አፍሪካ በአፓርታይድ የዘር መድልኦ አስተዳደር ውስጥ በነበረችበት ወቅት የአሁኑ ገዢ የፖለቲካ ማህበር ANC ወታደራዊ ክንፍ መጠሪያ ነበር፡፡

 

MK በዙማ እና በደጋፊዎቻቸው የተመሰረተ አዲስ የፖለቲካ ማህበር ነው፡፡

 

 

መቀመጫውን በትሪፖሊ ያደረገው የሊቢያ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱልሐሚድ ድቤይባ መኖሪያ ቤት በሮኬት ተስፈንጣሪ ቦንቦች መመታቱ ተሰማ፡፡

 

የድቤይባ መኖሪያ ቤት እንደተመታ የፀጥታ ሀይሎች በቤቱ አካባቢ በብዛት መሰማራታቸውን TRT አፍሪካ ፅፏል፡፡

 

በጥቃቱ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤት ላይ ጉዳት መድረሱ ታውቋል፡፡

 

በሰዎች ላይ ያጋጠመ ክፉ ነገር እንደሌለ በስም መጠቀስ ያልፈለጉ ሹም ተናግረዋል ተብሏል፡፡

 

በሊቢያ የቀድሞው መሪ የኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊ አስተዳደር ከ12 አመታት በፊት በትጥቅ አመፅ ከተወገደ ወዲህ አገሪቱ ሰላም እና መረጋጋት እንደራቃት ነው፡፡

 

በምስራቅ እና ምዕራብም እንደተከፋፈለች ትገኛች፡፡

 

የሊቢያው ፖለቲካዊ ቀውስ መቋጫ አላገኘም፡፡

 

 

ሩሲያ ዩክሬይንን በከባድ የሚሳየል ድብደባ ፋታ እየነሳቻት ነው ተባለ፡፡

 

የሩሲያ የሚሳየል ድብደባ በተለይም በዩክሬይን የኤሌክትሪክ የመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ PBS ፅፏል፡፡

 

በዚሁ ድብደባ እንደ ሐርኪቭ እና ኦዴሣ ያሉ የዩክሬይን ከተሞች በጨለማ ለመዋጥ ተገድደዋል ተብሏል፡፡

 

ችግሩ በተለይም በሐርኪቭ ከተማ የበረታ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

 

የዩክሬይኑ ጦርነት ከተጀመረ ከ2 አመታት በላይ ሆኖታል፡፡

 

የጦርነቱ መቆሚያ ምልክት በቅርብ አይታይም፡፡

 

 

የሶማሊያ ፌዴራላዊ መንግስት አካል ሆና የቆየችው ፑንትላንድ ከእንግዲህ ከሞቃዲሾ ጋር ያለኝን ማንኛውንም ዓይነት ግንኙነት አቋርጫለሁ አለች፡፡

 

የፑንትላንድ አስተዳደር ከእንግዲህ ከሶማሊያ ፌዴራላዊ መንግስት ጋር አንዳችም ግንኙነት አይኖረኝም ያለው የፌዴራሉ ምክር ቤት ህገ መንግስታዊ ማሻሻያ ማድረጉን ተከትሎ እንደሆነ ሆርሲድ ሚዲያ ፅፏል፡፡

 

በፌዴራሉ ፓርላማ ማሻሻያ የተደረገበት ጊዜያዊ ህገ መንግስት 12 አመታትን ያስቆጠረ ነበርተብሏል፡፡

 

የፑንትላድ አስተዳደር ነባሩ ጊዜያዊ ህገ መንግስት እንዳይነካ ሲያስጠነቅቅ መቆየቱን ዘገባው አስታውሷል፡፡

 

ለፌዴራል መንግስቱ እውቅና የነፈገው የፑንትላንድ አስተዳደር ከእንገዲህ ራሴን የቻልኩ ነፃ መንግስት ነኝ ማለቱ ተሰምቷል፡፡

 

የአስተዳደሩ ውሳኔ ለፑንትላንድ ግዛታዊ ምክር ቤት እንደሚቀርብ ታውቋል፡፡

 


የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

 

 

 

bottom of page