መጋቢት 15/2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች
- 13 minutes ago
- 2 min read
መጋቢት 15/2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ሹሞች ጋር በጦርነቱ ማብቂያ ጉዳይ ተነጋግረን ተግባብተናል ማለታቸውን የቴህራን ሹሞች በጭራሽ ሐሰት ነው አሉ፡፡
ትራምፕ የኢራንን የኤሌክትሪክ አውታሮች በጦር ለመመነቃቀር የነበራቸውን እቅድ በተጨማሪ 5 ቀናት ያራዘሙት ከዚሁ ንግግር በኋላ እንደነበር እወቁልኝ ብለው ነበር፡፡
የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ ግን ከአሜሪካ ሹሞች ጋር በየትም ቦታ በየትኛውም የመገናኛ ዘዴ የተደረገ ንግግር የለም ማለታቸው ቢቢሲ ፅፏል፡፡

ትራምፕ ከኢራን ሹሞች ጋር በተደረገ ንግግር የመካከለኛው ምስራቅ ልዩ መልዕክተኛቸው ስቴቭ ዊትኮፍ እና አማቻቸው ጃሬድ ኩችነር አሜሪካን በመወከል የተሳተፉበት ነበር ብለዋል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ኢራን የሆርሙዝን የባህር መተላለፊያ ሰርጥ ካልከፈተች የኤሌክትሪክ አውታሮቿን በሙሉ እደመስሳለሁ ሲሉ የ48 ሰዓት የጊዜ ገደብ አስቀምጠው ነበር፡፡
ኢራን አሁንም ድረስ የኤሌክትሪክ አውታሯ የሚነካ ከሆነ የአቅራቢያው አገሮች ወሳኝ የመሰረተ ልማት አውታሮች እንደማይተርፏት እየዛተች ነው፡፡
ጃፓን የሆርሙን ሰርጥ ለማስከፈት የጦር መርከቦቿን ለመላክ ተስማምታለች መባሉን የአገሪቱ የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ኪሃራ ሚኖሩ በጭራሽ ሐሰት ነው አሉ፡፡
ቀደም ሲል በተባበሩት መንግስታት የአሜሪካው አምባሳደር ማይክ ዋልትዝ ጃፓን የጦር መርከቦቿን ወደ ሆርሙዝ ለመላክ ተስማምታለች ሲሉ ለአሜሪካ ቲቪ ተናግረው እንደነበር አረብ ኒውስ ፅፏል፡፡
የጃፓኑ የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ግን ወደ ሆርሙዝ የጦር መርከብ ለመላክ የገባነው ቃል የለም ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
ቀደም ሲል የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጃፓን የጦር መርከቦቿን ወደ ሆርሙዝ እንድትልክ ይፋዊ ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡
በዚህ ጉዳይ ትራምፕ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን /ኔቶ/ አጋሮቻቸውን ሳይቀር በፈሪነት ሲወርፏቸው ሰንብተዋል፡፡
የጃፓን ሕገ መንግስት የአገሪቱን ጦር የባህር ማዶ ተሳትፎ እንደማይፈቅድ ይነገራል፡፡
በእስራኤል በተቃዋሚ መሪነታቸው የሚታወቁት አቪግዶር ሊበርማን አሜሪካ የኢራኑን ጦርነት ብታቆም እንኳ እኛ በውጊያው መቀጠል ይኖርብናል አሉ፡፡
የአቪግዶር ሊበርማን አስተያየት የተሰማው የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የተካሄደው ንግግር ፍሬያማ ነበር ማለታቸውን ተከትሎ እንደሆነ ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል፡፡
ሊበርማን አሜሪካ እንኳ ከጦርነቱ ብትወጣ እኛ ይበልጥ አጠንክረን ልንቀጥል ይገባል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጣምራ የጦር ድብደባ ከጀመሩ ከ3 ሳምንታት በላይ ሆኗቸዋል፡፡
ሊበርማን የኢራኑን መንግስታዊ አስተዳደር ምንቅርቅሩን ልናወጣው ይገባል ብለዋል፡፡
አቪግዶር ሊበርማን የእስራኤል ቤይትኑ የተሰኘው የፖለቲካ ማህበር መሪ እንደሆኑ መረጃው አስታውሷል፡፡
እስራኤል ባለፈው አመት ሰኔ ወርም ከኢራን ጋር ለ12 ቀናት የዘለቀ ከባድ ውጊያ አካሂዳ ነበር፡፡
በኬንያ ሆን ብለው ራሳቸውን ለመሰወር ሞክረዋል የተባሉት የአገሪቱ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራፋኤል ቱጁ በፖሊ ተይዘው ታሰሩ ተባለ፡፡
ራፋኤል ቱጁ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ምሽት ለነበረባቸው የሬዲዮ ቃለ መጠይቅ ከሾፌራቸው ጋር በመኪና ሲያመሩ እንደተሰወሩ የቤተሰብ አባሎቻቸው አመልክተው እንደነበር ቢቢሲ ፅፏል፡፡
ያም ሆኖ የፖሊስ መርማሪዎች የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተሰውረዋል በተባሉባቸው ጊዜያት ሁሉ በመኖሪያ ቤታቸው እንደነበሩ አረጋግጠናል ብለዋል፡፡
ቱጁ ወደ ሬዲዮ ጣቢያ ቀጠሯቸው ሲያመሩ አንድ መኪና ሲከታተላቸው ስለነበር ፈጥነው ራሳውን ለመሰወር መወሰናቸውን ተናግረዋል፡፡
ግለሰቡ በፍርድ ቤት እልባት ያላገኘ የንብረት ጉዳይ እንዳለባቸው ተሰምቷል ፡፡
ቀደም ሲል ቱጁ ጉልበተኛ የመንግስት ሹሞች ሐብት ፤ ንብረቴን ለመንጠቅ እያሴሩ ነው ብለው ነበር፡፡
በዚህ ጉዳይ ከኬንያ መንግስት በኩል የተሰማ አስተያየት የለም፡፡
የኔነህ ከበደ





Comments