መስከረም 26 2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች
- sheger1021fm
- Oct 7
- 2 min read
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጋዛ ሰላም ለማውረድ ከምን ጊዜውም የተሻለ እድል አለ ማለታቸው ተሰማ፡፡
የትራምፕ አስተያየት የተሰማው የእስራኤል እና የሐማስ ተደራዳሪዎች በግብፅ ሻርም ኤል ሼክ ቀጥተኛ ያልሆነውን ንግግር በሚያደርጉበት አጋጣሚ እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
አሜሪካም የጉዳዩን ተከታታዮች ወደ ሻርም ኤል ሼክ መላኳ ታውቋል፡፡
የካታር እና የግብፅ ሹሞች ቀጥተኛ ያልሆነው ንግግር አደራዳሪዎች ናቸው ተብሏል፡፡

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጋዛው የሰላም እቅዳቸው ላይ ለመስማማት የተሻለ እድል አለ ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
የታጋቾች እና የእስረኞች ልውውጡ በንግግሩ ቅድሚያ የተሰጠው ጉዳይ መሆኑ ታውቋል፡፡
የጋዛው ቀውስ ከተጀመረ ዛሬ 2ኛ ዓመቱን ደፍኗል፡፡
እስራኤል የጋዛ ዘመቻዋን የጀመረችው ሐማስ መራሽ የፍልስጤም ታጣቂዎች ወደ ደቡባዊ እስራኤል በመዝለቅ በድንገት ደራሽ ጥቃት 1 ሺህ 200 እስራኤላውያንን መግደላቸውን ተከትሎ ነበር፡፡
በጊዜው ፍልስጤማውያኑ ታጣቂዎች 251 ታጋቾችን ይዘው ወደ ጋዛ ተመልሰዋል፡፡
አሁን የቀሩት ታጋቾች 48 ሲሆኑ 20ዎቹ በሕይወት እንዳሉ ይገመታል፡፡
በእስራኤል የጋዛ ዘመቻ የተገደሉ ፍልስጤማውያን ብዛት ከ67,000 በላይ ደርሷል፡፡
የማዳጋስካሩ ፕሬዘዳንት አንድሬይ ራጆሊና አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሾሙ፡፡
ፕሬዘዳንቱ የጦር ሰራዊቱን ጄኔራል ሩፒን ፎርቱናት ዛፊሳምቦን በጠቅላይ ሚኒስትርነት የሾሙት ነባሩን ካቢኔ እንዳለ ከሀላፊነት ካባረሩ በኋላ ነው፡፡
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የተሾሙት በአገሪቱ በኤሌክትሪክ እና በውሃ አገልግሎት መቋረጥ እና መቆራረጥ ምክንያት የተቀሰቀሰው የወጣቶች ተቃውሞ በቀጠለበት አጋጣሚ እንደሆነ አናዶሉ ፅፏል፡፡
ፕሬዘዳንቱ በጠቅላይ ሚኒስትርነት የተሾሙት ዛፊ ሳምቦ ሁሉም ነገር ያስተካክሉታል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
በማዳጋስካር ተቃውሞው ባስከተለው ግጭት ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች ብዛት 22 መድረሱ በአልጀዚራ ዘገባ ተጠቅሷል፡፡
አለም አቀፉ የወንጀል ችሎት(ICC) በሱዳን ዳርፉር ግዛት በቀድሞ የጃንጃዊድ ሚሊሺያ መሪ ዓሊ ሙሐመድ ዓሊ አብዱራህማን ላይ በጦር ወንጀል እና በሰብአዊ ፍጡራን ላይ በተፈፀመ ግፍ የጥፋተኝነት ብይን አሳለፈ፡፡
ችሎቱ ግለሰቡ በበርካታ የጦር ወንጀሎች ጥፋተኛ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ማለቱን አልጀዚራ ፅፏል፡፡
ጃን ጃዊድ ከ20 አመታት በፊት በዳርፉር በተፈፀመ እልቂት የቀድሞው የሱዳን ፕሬዘዳንት ኦማር ሐሰን አልበሽር ደጋፊ የአረብ ታጣቂዎች ቡድን እንደነበር መረጃው አስታውሷል፡፡
የRSF ፈጥኖ ደራሽ ሀይልም ወደ አሁኑ ቁመናው የመጣው ከጃንጃዊድ ሚሊሺያ መሆኑ ይነገራል፡፡
ዓሊ ሙሐመድ ዓሊ አብዱራህማን እስከ እድሜ ልክ የሚዘልቅ እስር ቅጣት ሊፈረድበት እንደሚችል ተገምቷል፡፡
በአውስትራሊያ ሲድኒ በእሩምታ ተኩስ በ16 ሰዎች ላይ አካላዊ ጉዳት አድርሷል የተባለ ግለሰብ ተይዞ ክስ ተመሰረተበት፡፡
ግለሰቡ ከመኖሪያ ቤቱ ሆኖ በጎዳናው በሚያልፉ ተሽከርካሪዎች ላይ የእሩምታ ተኩስ ከፍቶ ነበር ተብሏል፡፡
በአውቶማቲክ ጠመንጃው ከመቶ በላይ ጥይቶችን መተኮሱን ገልፍ ኒውስ ፅፏል፡፡
ለእሩምታ ተኩስ የተገለገለበት የጦር መሳሪያ ያልተመዘገበ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
የዋስትና መብት መነገፉም ታውቋል፡፡
በግለሰቡ ላይ በፍርድ ቤት ክስ ቢመሰረትበትም ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራዎችን አደርጋለሁ ማለቱ ተሰምቷል፡፡
በአውስትራሊያ እንዲህ ዓይነቱ ወንጀል እምብዛም ያልተለመደ መሆኑን መረጃው አስታውሷል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s
👔LinkedIn ፡ https://tinyurl.com/tyfaekvx
Comments