መስከረም 26 2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች
- sheger1021fm
- Oct 6
- 2 min read
የሶማሊያው ፅንፈኛ ቡድን /አልሸባብ/ በርዕሰ ከተማዋ ሞቃዲሾ በሚገኝ እስር ቤት ላይ ጥቃት መፈፀሙ ተሰማ፡፡
በአልሸባብ ታጣቂዎች ጥቃት ደርሶበታል የተባለው የእስር ማዕከል በአገሪቱ ቤተ መንግስት አቅራቢያ የሚገኝ ነው መባሉን ቢቢሲ ፅፏል፡፡
ብዙ የአልሸባብ ቡድን ታጣቂዎችም ታስረውበት የሚገኝ ማዕከል ነው ተብሏል፡፡

ሰባት የአልሸባብ ታጣቂዎች በሞቃዲሾው የእስር ማዕከል ላይ ጥቃት ያደረሱት የመንግስትን ጦር ባልደረቦች የደምብ ልብስ አመሳስለው በመልበስ ነው ተብሏል፡፡
ከፍተኛ ፍንዳታ እና የተኩስ ልውውጥ እንደነበር ታውቋል፡፡
የሶማሊያ መንግስት ሁሉንም ጥቃት አድራሾች ገድለናቸዋል ማለቱ ተሰምቷል፡፡
ከመንግስት ጦር ወገን ስለ ተገደሉ ወይም ጉዳት ስለደረሰባቸው የጠቀሰው ነገር የለም፡፡
ብዙ ታሳሪዎችን አስመልጫለሁ ያለው አልሸባብ ከእርሱ ወገንስ ለደረሰው ጉዳት ያነሳው ነገር የለም፡፡
የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አርጋቸ ከእንግዲህ ከአለም አቀፉ የአቶሚክ ተቆጣጠሪ ድርጅት /IAEA/ ጋር ትብብራችንን መቀጠሉ ምንም አስፈላጊነት የለውም አሉ፡፡
የአርጋቺ አስተያየት የተሰማው ለኢራን ተነስቶላት የነበረው የተባበሩት መንግስታት ማዕቀብ ከ10 አመታት በኋላ ዳግም ስራ ላይ መዋሉን ተከትሎ እንደሆነ አልጀዚራ ፅፏል፡፡
ከ10 አመታት በፊት ለኢራን ማዕቀቡ የተነሳላት በጊዜው ከአለማችን ኃያላን ጋር ኒኩሊየር ነክ ስምምነት በመፈራረሟ ነበር፡፡
አሜሪካ በትራምፕ ቀዳሚ የአስተዳደር ዘመን ራሷን ከስምምነቱ አግልላለች፡፡
ኢራን ስምምነቱን አላከበረችም ባዮቹ ብሪታንያ ፣ ፈረንሳይ እና ጀርመን ባሳደሩት ግፊት ኢራን ዳግም ለተባበሩት መንግስታት ማእቀብ ተጋልጣለች፡፡
ምዕራባዊያን ኃያላን ኢራን የኒኩሊር ቦምብ ለመስራት እየተሯሯጠች ነው ሲሉ ይከሷታል፡፡
ኢራን የኃያላኑን አመኔታ ባታገኝም የኒኩሊየር መርሐ ግብሬ ለኤሌክትሪክ ማመንጫ እና ለሰላማዊ አገልግሎቶች የታለመ ነው የሚል መሟገቻ እንደምታቀርብ መረጃው አስታውሷል፡፡
የሩሲያው ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን አሜሪካ ለዩክሬይን ቶም ሐውክ የረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳየል የምታስታጥቅ ከሆነ መሻሻል አሳይቶ የነበረው ግንኙነታችን ይበልጥ ይደፈርሳል አሉ፡፡
ቀደም ሲል የዩክሬይኑ ፕሬዘዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ቶም ሐውክ ሚሳየሎችን ለመታጠቅ ለአሜሪካ ጥያቄ ማቅረባቸውን ለአክሲዮስ እንደተናገሩ አናዶሉ አስታውሷል፡፡
የአሜሪካው ምክትል ፕሬዘዳንት ጂ ዲ ቫንስም አገራቸው የዩክይኑን ፕሬዘዳንት ጥያቄ እያጤነችው መሆኑን አልሸሸጉም፡፡
የሩሲያው ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬይን ቶም ሐውስ ሚሳየሎችን ብትታጠቅም በጦር አሰላለፋችን እና ይዞታችን ላይ የሚያስከትለው ለውጥ አይኖርም ብለዋል፡፡
ሆኖም በሩሲያ እና በአሜሪካ መካከል መሻሻል ያሳየውን ግንኙነት ግን በእጅጉ ያደፈርሰዋል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
ቶም ሐውክ የረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳየል እስከ 2500 ኪሎ ሜትር ርቀት እንደሚምዘገዘግ ይነገራል፡፡
በኔፓል የደረሰ ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት በጥቂቱ 47 ሰዎችን ገደለ ተባለ፡፡
የጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት አደጋው የደረሰው በአገሪቱ የጣለውን ዶፍ ዝናብ ተከትሎ እንደሆነ አልጀዚራ ፅፏል፡፡
በጎርፍ እና በመሬት መንሸራተት አደጋው መሞታቸው ከተረጋገጠው ሌላ በርካቶች ደግሞ የደረሱበት ጠፍቷል ተብሏል፡፡
የደረሱበት የጠፋውን የማፈላለጉ የነፍስ አድን ተግባር መቀጠሉ ታውቋል፡፡
በአገሪቱ ዶፍ ዝናቡ እንደሚቀጥል የአየር ትንበያ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በብዙ አካባቢዎችም የጎርፍ እና የተጨማሪ መሬት መንሸራተት ሊደርስ እንደሚችል ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን መረጃው አስታውሷል፡፡
ወደ ጋዛ ሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ በጀልባ በመጓጓዝ ላይ እያሉ በእስራኤል ጦር የተያዙት አለም አቀፍ በጎ ፈቃደኞች እየተለቀቁ መሆኑን የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እወቁልኝ አለ፡፡
ባለፈው ሳምንት የእስራኤል ጦር ወደ ጋዛ በጀልባዎች በማምራት ላይ ከነበሩት በጎ ፈቃደኞች መካከል 500 ያህሉን ከነጀልባዎቻቸው እንደያዘ ቢቢሲ አስታውሷል፡፡
ከነዚህም መካከል 137ቱ ተለቀው ወደ ቱርክ ማምራታቸውን የእስራኤል የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በመግለጫው እወቁልኝ ብሏል፡፡
እስራኤል በጎ ፈቃኞቹን የያዘቻቸውን ከአለም አቀፍ የባህር አካል ነው በሚል ከተለያዩ አቅጣጫዎች ነቀፋ እና ውግዘት ደርሶበታል፡፡
በጎ ፈቃደኞቹን እስራኤል አዋኪዎች እና ጠብ አጫሪዎች ስትል ጠርታቸዋለች፡፡
2ኛ ዓመቱን የደፈነው የእስራኤል የጋዛ የጦር ዘመቻ በሰርጡ የከባድ ከባድ ሰብአዊ ቀውስ ማስከተሉ ይነገራል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s
👔LinkedIn ፡ https://tinyurl.com/tyfaekvx
Comments