መስከረም 23 2018 - ወጋገን ባንክ በስዊፍት የሚላክን ዓለም አቀፍ ክፍያ ወጋገን ሞባይል መተግበሪያን በመጠቀም በኦንላይን መከታተል የሚያስችላቸውን አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ተናገረ
- sheger1021fm
- Oct 3
- 1 min read
ወጋገን ባንክ በስዊፍት የሚላክን ዓለም አቀፍ ክፍያ ወጋገን ሞባይል መተግበሪያን በመጠቀም በኦንላይን መከታተል የሚያስችላቸውን አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ተናገረ፡፡
አገልግሎቱ በተለይም በገቢ እና ወጪ ንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ኮርፖሬት ደንበኞች ያገለግላል ተብሏል።

ደንበኞች በስዊፍት ክፍያ ሲፈፅሙ የክፍያ ትዕዛዝ በባንኩ ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ ገንዘቡ ለታለመበት ግለሰብ ወይም ተቋም እስከሚደርስ ድረስ ያለውን ሂደት በሚደርሳቸው ልዩ የመከታተያ ቁጥር አማካኝነት በመጠቀም በወጋገን ሞባይል መተግበሪያ በኩል በቀጥታ መከታተል እና ክፍያው መፈጸሙን ማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ወጋገን ባንክ የጀመረው የኦንላይን የስዊፍት ክፍያ መከታተያ ስርዓት ባንኩ ለደንበኞቹ ሲሰጥ የቆየውን ዓለም አቀፍ የክፍያ አገልግሎት ፈጣን፣ ግልፅነት የሰፈነበት፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና የበለጠ አስተማማኝ ያደርገዋል ሲል ባንኩ በላከልን መግለጫ አስረድቷል።
ደንበኞች ክፍያቸውን ወደ ባንኩ መምጣት ሳይጠበቅባቸው በስልካቸው መከታተል የሚያስችል መሆኑም ተነግሯል፡፡
በተያያዘም አዲሱ የኦንላይን ክፍያ መከታተያ ስርዓት ዓለም አቀፍ ክፍያዎችን ለታለመለት ዓላማ እንዲደርሱ በማስቻል የሀገሪቱን ገቢ እና ወጪ ንግድ ለማቀላጠፍ እንዲሁም አዋጪ እንዲሆን በማገዝ በኩል የላቀ አስተዋፅኦ ያበረክታል ተብሎለታል።
አገልግሎቱን ለማግኘት ደንበኞች የወጋገን ሞባይል መተግበሪያ ስር ስዊፍት የሚለውን አማራጭበመከተል እና ልዩ የኦንላይን ክፍያ መከታተያ ኮድ ቁጥራቸውን በማስገባት መጠቀም ይችላሉ ተብሏል፡።
ንጋቱ ሙሉ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s
👔LinkedIn ፡ https://tinyurl.com/tyfaekvx











Comments