መስከረም 19 2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች
- sheger1021fm
- Sep 29
- 2 min read

የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ካሚል ኢድሪስ የአለም ማህበረሰብ RSFን በአሸባሪነት ይፈረጅልን አሉ፡፡
በሌተና ጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ የሚመራው RSF ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ከሱዳን መንግስት ጦር ጋር ሲዋጋ ከ2 አመታት በላይ ሆኖታል፡፡
ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ጦርነቱ እስከተቀሰቀሰ ድረስ ሉአላዊ የሽግግር ምክር ቤት የተሰኘው አካል ምክትል ሰብሳቢ እንደበሩ አናዶሉ አስታውሷል፡፡
መንግስታዊ ካሚል ኢድሪስ RSF በአለም አቀፍ ደረጃ በአሸባሪነት ይፈረጅልን ያሉት ለተባበሩት መንግስት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ባደረጉት ንግገር ነው ተብሏል፡፡
ጦርነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰብአዊ ቀውሱን እያባባሰ መምጣቱ ይነገራል፡፡
እስካሁን የሱዳኑን ጦርነት ማስቆሚያ አንዳችም ፍንጭ አይታይም፡፡

የፍልስጤማውያኑ ታጣቂ ቡድን /ሐማስ/ እስራኤል በጋዛ ከተማ በምትፈፅመው ከባድ ድብደባ የተነሳ ሁለት ታጋቾች ያሉባትን ሁኔታ ለማወቅ ተስኖኛል አለ፡፡
ሐማስ እስከ ትናንት አመሻሹ ድረስ ባሉት 48 ሰዓታት ታጋቾቹ ያሉበትን ሁኔታ ማወቅ አልቻልኩም ማለቱን TRT ዎርልድ ፅፏል፡፡
እንደሚባለው እስካሁን በሐማስ እጅ 50 ያህል ታጋቾች ይገኛሉ፡፡
ከመካከላቸው 20ዎቹ በሕይወት እንዳሉ ይገመታል፡፡
የጋዛው የተኩስ አቁም ንግግር እና ድርድር ባለመሳካቱ ታጋቾቹን በፍልስጤማውያን እስረኞች ልዋጭ የማስለቀቁ እድል ተመናምኗል፡፡
እስራኤል ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በጋዛ ከተማ ሁለገብ የጦር ዘመቻዋን ማክፏቷ ይነገራል፡፡

የቬኒዙዌላ መንግስት ዜጎቹን በብዛት በነፍስ ወከፍ መሳሪያዎች እያስታጠቀ ነው ተባለ፡፡
የአገሪቱ ፕሬዘዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ቬኒዙዌላውያን አገራቸውን ለመጠበቅ ወደ ኋላ አይሉም ማለታቸውን ቢቢሲ ፅፏል፡፡
አሜሪካ የጦር መርከቦቿን ወደ ደቡባዊ ካሪቢያን ማስጠጋቷ በቬኒዙዌላውያን ዘንድ የመወረር ስጋት አሳድሯል፡፡
በቅርቡም የአሜሪካ ጦር መነሻቸውን ከቬኒዙዌላ ያደረጉ ሶስት ጀልባዎችን በመምታት 17 ሰዎችን መግደሉን መረጃው አስታውሷል፡፡
አሜሪካ ጀልባዎቹ አደገኛ እፅ ጭነው ወደ አሜሪካ በማምራት ላይ ነበሩ ብላለች፡፡
ቬኒዙዌላ ግን ጀልባዎቹ ሰላማዊ ሰዎችን ያሳፈሩ ነበሩ ስትል የአሜሪካን ክስ አጣጥለዋለች፡፡
በእርምጃው ስጋት የገባው የፕሬዘዳንት ኒኮላስ ማዱሮ መንግስት ሲቪል ዜጎቹን በብዛት የነፍስ ወከፍ የጦር መሳሪያ እያስታጠቀ መሆኑ ተሰምቷል፡፡

በአሜሪካ ኦሪዞና የደረሰ የጎርፍ አደጋ 4 ሰዎችን ገደለ ተባለ፡፡
በዚያ ጎርፍ እና የውሃ ሙላቱ 3 ከተሞችን እንዳጥለቀለቀ አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡
በጎርፉ ፍራቻም ብዙዎቹ የከተሞቹ ነዋሪዎች በየቤታቸው ጣራ ላይ ሆነው ለማሳለፍ ተገድለዋል ተብሏል፡፡
በኦሪዞና ጎርፍ ያጋጠመው በዚያ የጣለውን ዶፍ ዝናብ ተከትሎ መሆኑ ታውቋል፡፡
ጎርፉ ከገደላቸው በተጨማሪ በርካቶች የገቡበት እንዲጠፋ ምክንያት መሆኑ ታውቋል፡፡
ታላቅ የነፍስ አድን እና የመልሶ ማቋቋም ተግባር እየተከናወነ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
የኔነህ ከበደ የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
Comments