top of page

መስከረም 15 2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • Sep 25
  • 2 min read
ree

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአየር ክልላችን በሩሲያ የጦር አውሮፕላኖች ተጥሶብናል የሚሉ አባል የኔቶ አገሮች አውሮፕላኖቹን መትተው መጣል አለባቸው አሉ፡፡

ቀደም ሲል ኢስቶኒያ እና ሮማንያ የአየር ክልላችን በሩሲያ የጦር ጄቶች ተጥሶብናል የሚል ክስ ማሰማታቸውን ታይምስ ኦፍ ኢንዲያ አስታውሷል፡፡

ኢስቶኒያ እና ሮማኒያ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት አባል አገሮች ናቸው፡፡

የኔቶ አባል አገሮች በሩሲያ ላይ ተመሳሳይ ክሳቸውን እየደጋገሙት ነው፡፡

ሩሲያ የጦር ጄቶቿ ወደ ኔቶ አባል አገሮች የአየር ክልል በጭራሽ አልገቡም እያለች ነው፡፡

ክሱንም ነገር ማጋጋያ ነው ስትል ማጣጣሏን መረጃው አስታውሷል፡፡


ree

የኢራኑ ፕሬዘዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን አገሬ የኒኩሊየር የጦር መሳሪያ የመስራት ፍላጎቱም ሆነ ዓላማ የላትም አሉ፡፡

ፔዜሽኪያን የኒኩሊየር የጦር መሳሪያ አያሻንም ያሉት ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ባደረጉት ንግግር እንደሆነ ጄሩሳሌም ፖስት ፅፏል፡፡

በኢራን ላይ የተባበሩት መንግስታት ማእቀብ ዳግም ሊጫንባት እየተቃረበ ነው ተብሏል፡፡

በኢራን ላይ ዳግም የአለም አቀፋዊው ድርጅት ማእቀብ የሚጣልባት በብሪታንያ ፣ በጀርመን እና በፈረንሳይ ጎትጓችነት መሆኑ ታውቋል፡፡

ኢራን ታራምደዋለች በተባለው የኒኩሊየር መርሐ ግብር የተነሳ ከጥቂት ወራት በፊት ከእስራኤል ጋር ወደ ከባድ ግጭት አምርታ ነበር፡፡

ምዕራባዊያን ኃያላን ኢራን የኒኩሊየር ቦምብ ለመስራት እየተሯሯጠች ነው ሲሉ ይከሷታል፡፡

ኢራን ግን የሚያምናት ባታገኝም መርሐ ግብሬ ለኤሌክትሪክ ማመንጫ እና ለሰላማዊ አገልግሎቶች የታለመ ነው የሚል መሟገቻ ታቀርባለች፡፡

ree

ከየመን መሰንዘሩ በተነገረ የሰው አልባ በራሪ አካል /ድሮን/ ጥቃት በእስራኤሏ ደቡባዊ ከተማ ኤይላት በጥቂት 19 ሰዎች የተለያየ ደረጃ አካላዊ ጉዳት እንደገጠማቸው የህክምና ምንጮች ተናገሩ፡፡

ጥቃቱ ከደረሰባቸው መካከል ሁለቱ ብርቱ ጉዳት እንደገጠማቸው ይድዮት አህሮኖት የተሰኘውን የእስራኤል ጋዜጣ ዋቢ ያደረገው አናዶሉ ፅፏል፡፡

የእስራኤል ጦርም የድሮን ጥቃቱ መፈፀሙን አረጋግጧል ተብሏል፡፡

ዝርዝሩን ግን እንዳላብራራው ተጠቅሷል፡፡

እስራኤል የጋዛ የጦር ዘመቻዋን ከከፈተች ወዲህ የየመን ሁቲዎች ለፍልስጤማውያን አጋርነታቸው ለማሳየት ወደ እስራኤል ሚሳየል እየተኮሱና አጥቂ ሰው አልባ በራሪዎችን እየሰደዱባት ነው፡፡

እስራኤልም በተደጋጋሚ በሁቲዎቹ ይዞታ ላይ ከባባድ ጥቃቶችን ስታደስባቸው ቆይታለች፡፡

ስለ ኤይላቱ ጥቃት የየመን ሁቲዎች ፈጥነው አስተያየት አልሰጡም ተብሏል፡፡

ርዕሰ ከተማዋ ሰንዓን እና የየመንን ሰሜናዊ ክፍል የሚያስተዳድሩት ሁቲዎቹ የኢራን ሁነኛ አጋሮች መሆናቸው ይነገራል፡፡

ree

ከአሜሪካ ወደ ጋና ከተባረሩት የ3ኛ አገር ስደተኞች ወደ ቶጎ ተልከዋል ተባለ፡፡

ጋና ቀደም ሲል 11 ከአሜሪካ ተባራሪዎችን መቀበሏን ቢቢሲ አስታውሷል፡፡

ከአስራ አንዱ ተባባሪዎች መካከል ስድስቱ ወደ ቶጎ መላካቸውን ጠበቆቻቸው እንደተናገሩ ተሰምቷል፡፡

ወደ ቶጎ ከተላኩት መካከል የአገሪቱ ዜጎች ሶስቱ ብቻ ናቸው ተብሏል፡፡

ይሁንና ከአሜሪካ ተባራሪዎቹን በተመለከተ ከጋናም ሆነ ከቶጎ መንግስት በኩል የተሰማ አስተያየት እንደሌለ በመረጃው ተጠቅሷል፡፡

ጋና ተጨማሪ 40 ከአሜሪካ ተባራሪ የ3ኛ አገር ስደተኞችን ለመቀበል እየተዘጋጀች ነው ተብሏል፡፡

በአንዳንዶቹ የአፍሪካ አገሮች ከአሜሪካ ተባራሪዎቹን የመቀበሉ ሒደት ተቃውሞውን ጭምር እያስከተለ መሆኑን መረጃው አስታውሷል፡፡

ree

የስፔኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ሰብአዊ እርዳታ ጭነው በጀልባዎች ወደ ጋዛ በማምራት ላይ የሚገኙትን በጎ ፈቃደኞችን በጦር መርከብ እናጅባቸዋለን አሉ፡፡

ቀደም ሲል ጣሊያንም በጎ ፈቃደኞቹን በጦር መርከብ ጥበቃ አደርግላቸዋለሁ ማለቷን ሬውተርስ አስታውሷል፡፡

ሁለቱ አገሮች የበጎ ፈቃደኞቹን ጀልባዎች ለመጠበቅ የጦር መርከቦቻችንን እናሰልፋለን ያሉት በግሪክ የባህር ዳርቻ የድሮን ጥቃት ከተሰነዘረባቸው በኋላ ነው ተብሏል፡፡

50 ያህሉ ጀልባዎች ከ45 አገራት የተውጣጡ በጎ ፈቃደኞችን ያሳፈሩ መሆኑ ታውቋል፡፡

በጎ ፈቃደኞቹ ሰብአዊ እርዳታዎችን ጭነው ወደ ጋዛ በማምራት ላይ የሚገኙት በዚያ በእስራኤል የጦር ዘመቻ አሳራቸውን ለሚያዩት ፍልስጤማውያን ርሕራሔያቸውን ለማሳየት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

በጎ ፈቃደኞቹ በጋዛ ለፍልስጤማውያ ምግብ እና ሰብአዊ እርዳታ ከማቅረብ በስተቀር የተለየ ዓላማ የላቸውም ተብሏል፡፡

 የኔነህ ከበደ


Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page