መስከረም 13 2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች
- sheger1021fm
- Sep 23
- 2 min read
የደቡብ ሱዳኑ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዘዳንት ሪያክ ማቻር የፍርድ ሒደት ትናንት ተጀመረ፡፡
ማቻር በብርቱ ብርቱ ወንጀሎች የተከሰሱት ከመንፈቅ በፊት በናሲር በሚገኝ የመንግስት ሰራዊት የጦር ሰፈር ላይ ከተፈፀመ ጥቃት ጋር በተያያዘ እንደሆነ አፍሪካ ኒውስ ፅፏል፡፡
ከዚያን ጊዜ አንስቶ ማቻር በቁም እስር ላይ እንደነበሩ ተጠቅሷል፡፡

ጥቃት አድራሹ በተለምዶ ዋይት አርሚ የተሰኘው እና ከማቻር ጋር ቁርኝት ያለው የኑዌር ወጣቶች ታጣቂ ቡድን መሆኑ ይነገራል፡፡
ብዛታቸው ምን ያህል እንደሆነ ባይጠቀስም የማቻር አባሪ ተባባሪዎች ናቸው የተባሉ ሌሎች ግለሰቦችም አብረው ችሎት መቅረባቸው ታውቋል፡፡
በማቻር እና አባሪ ተባባሪዎቻቸው ናቸው በተባሉ ግለሰቦች ላይ በግድያ ፣ በአሸባሪነት እና መንግስትን አደጋ ላይ በመጣል ብርቱ ብርቱ ክሶች እንደቀረቡባቸው ተጠቅሷል፡፡
የፍርድ ሒደቱ ጅማሬ በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት ሽፋን ማግኘቱን መረጃው አስታውሷል፡፡
የጅቡቲው ፕሬዘዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌ የረጅም ጊዜ አማካሪ እና ቃል አቀባያቸው አሌክሲስ ሞሐመድ ከእንግዲህ በሀላፊነቴ አልቀጥልም አሉ፡፡
አሌክሲስ ሞሐመድ ሀላፊነታቸውን የለቀቁት የጂቡቲ ዲሞክራሲ እየተንሸራተተ ነው የሚል ምክንያት በማቅረብ እንደሆነ AFP ፅፏል፡፡
የቀድሞው መንግስታዊ ቃል አቀባይ በአገሪቱ ምዝበራ እና ንቅዘቱ እየከፋ ነው ማለታቸው ተጠቅሷል፡፡
አሌክሲስ ሞሐመድ ሀላፊነታቸውን የለቀቁት በአገሪቱ ከአመት ባልበለጠ ጊዜ ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ይከናወናል ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት ነው፡፡
አገሪቱን ለ26 ዓመታት የመሯት ኢስማኤል ኦማር ጌሌ በመጪውም ምርጫ የመፎካከር ፍላጎት አላቸው ተብሏል፡፡
ሆኖም ጌሌ በምርጫው ተፎካካሪነት ለመቅረብ ህገ መንግስታዊ ማሻሻያ እንደሚያሻቸው መረጃው አስታውሷል፡፡
ኢስቶኒያ ባለፈው ሳምንት በሩሲያ የጦር ጄቶች የአየር ክልሌ ተጥሶብኛል ማለቷን ሞስኮ በጭራሽ አላደረኩትም አለች፡፡
የሩሲያ ሹሞች የኢስቶኒያን ክስ ነገር ማጋጋያ ሲሉ መጥራታቸውን አልጀዚራ ፅፏል፡፡
ኢስቶኒያ ለክሷ አንዳችም ተጨባጭ ማስረጃ ማቅረብ አትችልም ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
ቀደም ሲል ፖላንድ ፣ ከዚያም ሮማኒያ የአየር ክልላችን በሩሲያ አጥቂ ሰው አልባ በራሪ አካላት /ድሮኖች/ ተጥሶብናል የሚል ክስ ሲያሰሙ ሰንብተዋል፡፡
ፖላንድ ፣ ሮማንያ እና ኢስቶኒያ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት /ኔቶ/ አባል አገሮች ናቸው፡፡
የዩክሬይኑ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ በሩሲያ እና በኔቶ መካከል ከጊዜ ወደ ጊዜ የጦር ፍጥጫው እያየለ መምጣቱ ይነገራል፡፡
በኮንጎ ኪንሻሣ ካሳይ ግዛት ከተቀሰቀሰ የሰነበተው የኢቦላ ወረርሽኝ የገደላቸው ሰዎች ብዛት ወደ 31 ከፍ አለ፡፡
እስካሁን በግዛቲቱ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ብዛት 38 መድረሱን አፍሪካ ኒውስ ፅፏል፡፡
ባለፈው ሳምንት በካሳይ ግዛት አዲሱ የኢቦላ ወረርሽኝ የገደላቸው ሰዎች ብዛት 16 ነበር፡፡
በኢቦላ ከተያዙት እና በበሽታው ሕይወታቸው ካለፈው ሰዎች ጋር ቅርበት የነበራቸውን የመለየቱ ተግባር መቀጠሉ ታውቋል፡፡
እስከ ትናንትም 900 ሰዎች መለየታቸው ታውቋል፡፡
የወረርሽኙ የስርጭት አድማስ እየሰፋ ነው ተብሏል፡፡
ኮንጎ ኪንሻሣ የኢቦላ ወረርሽኝ የሚደጋገምባት አገር ነች፡፡
የአሁኑ የካሳይ ግዛት የኢቦላ ወረርሽኝ ባለፉት 50 ዓመታት ለአገሪቱ 16ኛዋ እንደሆነ መረጃው አስታውሷል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
Comments