ሐምሌ 30 2017 - በኢትዮጵያ መንግስት እና በሌሎች ተቋማት የሚወጡ ምጣኔ ሀብትን የተመለከቱ ቁጥራዊ መረጃዎች በዚህ ደረጃ እንዴት ሊራራቁ ቻሉ?
- sheger1021fm
- Aug 6
- 2 min read
መንግስት ዓመታዊ በጀቴ በ200 እጥፍ አድርጓል፣ የግሽበት ምጣኔውንም ወደ 15 በመቶ እንዲቀንስ አድርጌአለሁ ብሏል፡፡
በምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ የሀገር ቤትና የውጪ ተቋማት ደግሞ የሚጠቅሱት ቁጥር ከዚህ ይለያል፡፡
እንደ ምሳሌም የአለም ባንክ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሁኔታ ለመተንበይ ያስቸግረኛል የሚል ሪፖርት በቅርቡ አውጥቷል፡፡
የዋጋ ግሽበቱ 20 በመቶ ነው ያሉም አሉ፡፡ እንዲህ ያለው ልዩነት ከየት የመጣ ነው?
በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ያሉ ለውጦችን በተመለከተ በመንግስት እና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት የሚሰጡ መረጃዎች ሲለያዩ፤ አንዳንዴም ሲጣረሱ ይታያል።
ለምሳሌም መንግስት የሀገሪቱ በጀት በያመቱ እያደገ መምጣቱን ፤ ጥቅል ሀገራዊ ምርት ከፍ ማለቱን ፤ የብድር ጫና ደግሞ መቀነሱን በተደጋጋሚ ይገልፃል።
በኢትዮጵያ የዜጎች የነብስ ወከፍ ገቢ ከሰሃራ በስተደቡብ ካሉ ሀገራት ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚጠቀስ ሆኗልም ይላል።
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሞያዎች ማህበር በበኩሉ በቅርቡ አደረኩት ያለውን ጥናት ጠቅሶ ጥቅል ሀገራዊ ምርቱ እያደገ ቢሆንም ፤ የዜጎች የነብስ ወከፍ ገቢ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቀለ መጥቷል ሲል ተናግሯል።
በተለይም ከጎርጎርሳውያኑ 2019 ጀምሮ የጥቅል ሀገራዊ ምርት እና የዜጎች የነብስ ወከፍ ገቢ ዕድገት በተጻራሪ መንገድ እየሄዱ ናቸውም ብሏል።
መንግስት በቅርቡ ለ2018 ያጸደቀው 1.93 ትሪሊየን ብር ከእስከ አሁኑ ሁሉ ከፍተኛው እንደሆነ መናገሩም የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ መንግስት በጀት ባለፉት 20 ዓመታት በ200 በመቶ ማደጉን የሚጠቅሰው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሞያዎች ማህበር በበኩሉ፤ በገንዘብ ትክክለኛ የመግዛት አቅም ሲተመን ግን በጀቱ እያደገ ሳይሆን እየቀነሰ ነው የመጣው ብሏል።
አለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ( #IMF ) ደግሞ በኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበቱ ባለንበት የጎርጎርሳውያኑ 2025 20 በመቶ ሆኖ ይቀጥላል የሚል ሪፖርት ከወራት በፊት አውጥቷል።
ግሽበቱን እስከ ጎርጎርሳውያኑ 2028 ድረስ ወደ ነጠላ አሃዝ ማውረድ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል ሲልም ትንበያውን አስቀምጧል።
የአይ ኤም ኤፍ ሪፖርት የተሰማው ‘’የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ’’ ባለፈው መጋቢት ወር ላይ ዓመታዊ የዋጋ ግሽበቱ የካቲት ላይ 15 በመቶ ደርሷል ካለ በኋላ ነው።
የአለም ባንክ ደግሞ በጎርጎርሳውያኑ አቆጣጠር ከሃምሌ 2025 እስከ ሰኔ 2026 ባለው ጊዜ የሚኖረውን የሀገራት የኢኮኖሚ ሁኔታ ሲሰረዝር የኢትዮጵያውን ለመተንበይ አስቸጋሪ በሚል ገልፆታል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ግን ኢኮኖሚ በቀጣዩ ዓመት በ8 .9 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው የተናገሩት። ለመሆኑ እንዲህ አይነት የመረጃ መጣረሶች በምን ምክንያት ይመጣሉ? መረጃዎቹ ሲዘጋጁ ሁሉም ሊከተሏቸው የሚገቡ ሳይንሳዊ መንገዶችስ አይኖሩ ይሆን?
ጥያቄውን የቀረብንላቸው የምጣኔ ሃብት ባለሞያው ዶክተር አቡሌ መሃሪ መረጃው ከሚነገርበት አውደ ጋር ይገናኛል ብለውናል።
የኢኮኖሚ ለውጦችን ለማወቅ የሚመረጡ መንገዶችም የልዩነቱ ሌሎች ምክንያቶች እንደሆኑ ዶክተር አቡሌ ተናግረዋል።
የዋጋ ግሽበት ፤ የውጭ ምንዛሪ ክምችት እና የምንዛሪ ተመንን በመጠቀም የሚዘጋጁ መረጃዎች ውጤታቸው ይለያያል ብለዋል።
አንዱ መረጃ በሌላ መረጃ ላይ ተመስርቶ እንደሚዘጋጅ ያስታወሱት ዶክተር አቡሌ አንዳንዴ ይሄም የልዩነቱ መነሻ ይሆናል ብለዋል።
ለአብነትም የኢትዮጵያን ህዝብ ቁጥር በተመለከተ የተለያዩ ተቋማት የተለያየ መረጃ ያወጣሉ ያንን የተለያየ መረጃ በመጠቀም የሚሰራ ጥናት ውጤቱ እንዲሁ ይለያያል ብለዋል።
በቅርብ ጊዜ የተካሄደ እና ትክክለኛውን ብዛት የሚያሳይ ቆጠራ አለመኖሩ የችግሩ መነሻ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
የኢኮኖሚ ዕድገቱን መሬት ላይ ከሚታዩ የመሰረት ልማት አውታሮች ዝርጋታ ጋር አያይዘው የሚያቀርቡትም አሉ።
ሌሎች ደግሞ ዕድገቱ በህብረተሰቡ ኑሮ ላይም ለውጥ ካላመጣ እንደምን ዕድገት ሊባል ይችላል ይላሉ።
መንግስት በበኩሉ የዜጎች ህይወትም ቢሆን መሻሻል እያሳየ ይገኛል ሲል ይመልሳል።
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ….. https://www.mixcloud.com/ShegerFM/45745745/
ንጋቱ ረጋሳ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyu.com/ycxjmm3s












Comments