ሐምሌ 29 2017 - የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዘንድሮ በሀገር ውስጥ በረራ 28 ሚሊየን ዶላር ከሰርኩ አለ።
- sheger1021fm
- Aug 5
- 2 min read
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዘንድሮ በሀገር ውስጥ በረራ 28 ሚሊየን ዶላር ከሰርኩ አለ።
አየር መንገዱ በሀገር ውስጥ ያለውን ዋጋ ለማረጋጋትም መለዋወጫዎችን በውጭ ምንዛሪ እየገዛሁ ጫናውን ተቋቁሜ ቆይቻለሁ ብሏል።
ይህ የተሰማው የኢትዮዽያ አየር መንገድ ዘንድሮ ይህን ሁሉ ፈተና አልፌ በአጠቃላይ 7.6 ቢሊየን ዶላር ገቢ አግኝቻለሁ ባለበት ጊዜ ነው።
የዶላር ምንዛሪ ከሁለት እጥፍ በላይ ቢያድግም፤ የሀገር ውስጥ በረራ አገልግሎት ለመስጠት ከጥቃቅን ጭማሪ በቀር የተጋነነ ጭማሪ አልተደረገም እንደውም 28 ሚሊየን ዶላር ከስሬያለሁ ብሏል።
ይህ አሰራርም እንደማይቀጥል የኢትዮዽያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቦሌ አየር ማረፍያ፤ አውሮፕላን ሲነሳ እና ሲያርፍ ያለኝ የደህንነት ስጋትም ከፍተኛ ነው ብሏል።
አየር መንገዱ ስጋቴ እየጨመረ ነው ብሎ በምክንያትነት ያስቀመጠው፤ የአሞራ ግጭት ቁጥር መጨመርን ነው።
በቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፍያ አካባቢ በርካታ አሞራዎች እየጨመሩ ነው፤ ይህም የደህንነት ስጋቴን ከፍተኛ አድርጎታል ሲሉ ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ መስፍን ጣሰው ስጋታቸውን ጠቅሰዋል።
አየር መንገዱ ይህን ችግር ለመፍታትም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር እየመከርኩ ነው ብሏል።
አውሮፕላን የሚያርፍበት እና የሚነሳበት ቦሌ አለም አቀፍ ኤርፖርት አካባቢ በስፋት ያሉ ቆሻሻ ቦታዎች፣ ፍሳሽ ያለበት ቦታ፣ እርድ የሚከናወኑበት እና ሌሎች በራሪ አሞራዎችን የሚስብ ከባቢ ፈፅሞ እንዳይኖር ከሚመለከታቸው ጋር እየሰራ መሆኑን አየር መንገዱ ተናግሯል።
የኢትዮዽያ አየር መንገድ የአውሮፕላን የመለዋወጫ ችግሩ እየተሻሻለ ቢሆንም፤ አሁንም ከፍተኛ የአውሮፕላን መለዋወጫ እጥረት በማጋጠሙ እቃ ማቅረብ እያቃተን ማብረር የነበረብን አውሮፕላኖች ከመሬት እየዋሉ ነው ብሏል።

በተለይ የሀገር ውስጥ በረራ የሚገለገልባቸው QR-400 የተባለ አውሮፕላን ከፍተኛ የመለዋወጫ እጥረት እያጋጠመው መሆኑን ሰምተናል።
የሀገር ውስጥ በረራን በተመለከተ ዋጋው ውድ ነው አገልግሎቱም እንዲቀላጠፍ ምን እየሰራችሁ ነው ተብለው የተጠየቁት ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ የአውሮፕላን እጥረት እያጋጠመ በመምጣቱ አገልግሎቱን መስጠት በምንችለው መጠን እየሰጠን አይደለም ነገር ግን አንዳንዴ ለአለም አቀፍ ያዘጋጀናቸውን አውሮፕላኖች እናበራለን ብለዋል።
ዋጋውን በተመለከተም የሀገር ውስጥ በረራ ዋጋ የዶላር ምንዛሪ ከሁለት እጥፍ በላይ ቢያድግም አየር መንገዱ ዘንድሮ 28 ሚሊየን ዶላር ከስሬያለሁ፤ እንዲህም እየተሰራ አይቀጥልም ተብሏል።
የሀገር ውስጥ በረራውን ከፍ ለማድረግም አዳዲስ አውሮፕላኖችን ለማምጣት ጥናት እያደረኩ ነው ብሏል።
ዘንድሮ ይህን ሁሉ ፈተና አልፌ በአጠቃላይ 7.6 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማግኘቱን ተናግሯል።
ይህም ከባለፈው አመት ጋር ሲነፃፀር ስምንት በመቶ እድገት ማሳየቱን ሰምተናል።
አየር መንገዱ አለም አቀፍ ስራውን ለማስፋት ኤር ኮንጎ ከሚባል አየር መንገድ ጋር ሽርክና አቋቁሜ አገልግሎት እየሰጠሁ ነው ብሏል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በፀጥታ እና በሌሎች ምክንያቶችም ወደ ኤርትራ፤ ጎማ ከተማና ሌሎች በእቅዳችን ለመብረር ብናስብም በረራ ተስተጓጉሏል ወይም ታጥፏል ተብሏል።
በዚህም የኢትዮዽያ አየር መንገድ በኤርትራ በሚሊየን ዶላር የሚቆጠር የትኬት ሽያጭ ክፍያ ማስለቀቅ እንዳልተቻለ አቶ መስፍን አስረድተዋል።
ይህንንም የውጭ ምንዛሪ ለማስለቀቅ በፍርድ ቤት ብንሟገትም ነገሩ የፖለቲካ ጉዳይ በመሆኑ ማስለቀቅ አልተቻለም ብለዋል።
የኢትዮዽያ አየር መንገድ በዘንድሮ ዓመት 13 ዘመናዊ አውሮፕላኖች ወደ ስራ ማስገባቱን ሰምተናል።
አየር መንገዱ በዘንድሮ የስራ አፈፃፀም 15.2 ሚሊየን አለም አቀፍ ደንበኞችን አጓጉዣለሁ ብሏል።
የሀገር ውስጥ በረራን ጨምሮ ዘንድሮ በአጠቃላይ 19 ሚሊየን ደንበኞች ማጓጓዙን ሰምተናል።
ይህም ከአምናው ሲወዳደር እድገቱ 11 በመቶ ደርሷል ተብሏል።
በካርጎ ጭነት ከ700,000 ቶን በላይ አጓጉዘናል ያሉት አቶ መስፍን ይህም ከአምናው ዘጠኝ በመቶ አድጓል ብለዋል።
ለ5,000 ሰራተኞች መኖሪያ ቤት እየሰራን ነው ያለው አየር መንገዱ፤ ቤቶቹ በሚቀጥለው ዓመት ይጠናቀቃል ተብሏል።
የደንበኞች አገልግሎትን ለማሻሻል ብዙ ስራዎች ተሰርቷል ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ ቦሌ አውሮፕላን ማረፍያ የማስፋፍያ ስራ ተሰርቶ አገልግሎት እየሰጠ ነው፤ ይህም መንገደኞች የነበረባቸውን መጨናነቅ ፈትቶላቸዋል ተብሏል።
ተህቦ ንጉሴ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyu.com/ycxjmm3s











Comments