ሐምሌ 28 2017 - ለማህበራዊ ትስስር የበዙ ዕሴቶች እንዳላት የሚነገርላት ኢትዮጵያ
- sheger1021fm
- Aug 4
- 2 min read
ለማህበራዊ ትስስር የበዙ ዕሴቶች እንዳላት የሚነገርላት ኢትዮጵያ በትምህርት ሥርዓቷ አካታ ስላልሰራች በተለይ አሁን በትምህርት ላይ ያሉ ልጆች በተለያዩ ትምህርቶች እና በክህሎት የተሻሉ ቢሆኑም በማህበራዊ እሴቶች ግን ደካማ መሆናቸውን ጥናት አሳይቷል፡፡
ሰዎች በማህበራዊ እሴት እንዲሁም በሰብአዊ ልማት ደካማ ከሆኑ እርስ በርስ የመተማመን እና የመስማማት እድላቸው የጠበበ ነው ተብሏል፡፡
ቀጣሪ ተቋማት የሠራተኞቻቸውን ዕውቀት እና ክህሎት ለማሳደግ ስልጠናዎችን ያዘጋጃሉ።
ምርታማነታቸው እና ተወዳዳሪነታቸውንም ከፍ ለማድረግ ይሞክራሉ።
በዚህ መልኩ የሚደረግ የሰብአዊ ልማት ስራ የታሰበውን ለማሳካት ማገዙ ባይካድም ብቻውን ግን በቂ እንዳልሆነ የዘርፉ ባለሞያዎች ይናገራሉ።
ሰዎች የጋራ እሴት የሚያዳብሩበት መንገድም አብሮ ሊታሰብ እንደሚገባ ከእነዚሁ ሞያተኞች አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር ይልማ ገብረማርያም ያነሳሉ።
ማህበራዊ ልማት ሰዎች ያላቸው የጋራ እሴት እና የእርሰ በርስ ትስስር እንደሆነ የሚጠቅሱት የደቡባዊ ኮኔክ ቲከት ግዛት ፤ ዩኒቨርስቲ መምህር ፕሮፌሰር ይልማ ከሰብአዊ ልማት በእጅጉ የተሳሰረ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በአዲስ አበባ በሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሰብአዊ ልማት እና ማህበራዊ ልማት እንዴት ተጣጥመው እየተሰጡ ነው የሚለውን ለማወቅ ጥናት ማድረጋቸውን ፕሮፌሰር ይልማ ነግረውናል።
በጥናቱ ከአስሩም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 472 የተፈጥሮ እና ማህበራዊ ሣይንስ ተማሪዎች ተሳትፈዋል ብለዋል፡፡
በውጤቱ የሰብአዊ ልማት መገለጫ በሆኑት ክህሎት እና ዕውቀት ተማሪዎች የተሻሉ ሆነው ተገኝተዋል ነው ያሉን።
አብሮነት እና ማህበራዊ ትስስር ላይ ግን ውጤታቸው ዝቅተኛ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ጉዳዩ ከሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት ጋርም እንደሚያያዝ ፕሮፌሰር ይልማ ተናግረዋል።
ሰዎች ዕውቀት እና ክህሎት ስላላቸው ብቻ ምርታማ ሊሆኑ አይችሉም፤ ያንን ዕውቀታቸውን የጋራ እሴትና ግብ ይዘው ሊሰሩበት ይገባል ብለዋል።
በትምህርት ቤት ያሉ ወጣቶችን የማሀበራዊ ልማት ዕውቀት ለማሳደግ የስነ ምግባር እና ስነ ዜጋ ትምህርት በተጠናከረ መልኩ መሰጠት እንዳለበትም ፕሮፌሰር ይልማ ተናግረዋል።
ትምህርቱ ከዚህ ቀደም እንደነበረው የፖለቲካ አስተሳሰብ የተጫነው ግን ሊሆን አይገባም ብለዋል።
የትምህር ባለሞያዎች የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት በተለይ ስርአተ ትምህር ቀረጻ ላይ በተለይ ትኩረት እንዲሰጡ ፕሮፌሰር ይልማ ጠይቀዋል።
መንግስትም የሚያስበው የኢኮኖሚ ዕድገት ዕውን እንዲሆን የማህበራዊ ልማት አስተዋጽኦ ከፍ ያለ መሆኑን መረዳት አለበት ብለዋል።
ውጤቱ በቶሎ የሚታይ እንዳልሆነም ግን ማወቅ እንደሚያስፈልግ ፕሮፌሰሩ ጨምረው ተናግረዋል።
በአለም አቀፍ መለኪያም የኢትዮጵያ በማህበራዊ ልማት በኩል ያላት ደረጃ ዝቅተኛ ከሚባሉት ሀገራት ተርታ እንደሆነ ሠምተናል።
ንጋቱ ረጋሣ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s












Comments