ሐምሌ 22 2017 - የምሽት የንግድ ስራን አስገዳጅ የሚያደርገው ደምብ ዝርዝር የአፈፃፀም መመሪያ ሳይወጣለት መተግበር መጀመሩ ተነገረ
- sheger1021fm
- Jul 29
- 2 min read
የምሽት የንግድ ስራን አስገዳጅ የሚያደርገው ደምብ ዝርዝር የአፈፃፀም መመሪያ ሳይወጣለት መተግበር መጀመሩ ተነገረ፡፡
በከተማዋ ያሉ የንግድ ቤቶች እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት ከ30 እንዲሁም ታክሲዎችን ጨምሮ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት እንዲሰሩ መመሪያው ያስገድዳል፡፡
የደምቡን መውጣት ተከትሎ ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር በተደረጉ ውይይቶች በነጋዴው ወገን ሊያሰራ የማይችል ነው፤ የምንሰራው በከተማው መሃል የምንኖረው ግን በከተማው ዳርቻ ነው የመስሪያ ቦታችንንና መኖሪያችን በጣም የተራራቀ በመሆኑ አምሽተን ለመስራት የደህንነት ስጋቶች አሉብን፤ አምሽቶ መስራት ተጨማሪ የሰው ሃይል መቅጠር ስለሚጠይቅ ለተጨማሪ ወጪ እንዳረጋለን፤ ማህበረሰቡ በምሽት የመገበያየት ልምድ ስለሌለው ገዢ በማጣት እንከስራለን ለእነዚህ ስጋቶች መንግስት ዋስትና ይስጠን የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎች ሲቀርቡ ቆይተዋል።
ደምቡ በተለይ በነጋዴዎች ከፍተኛ ትችት ሲሰነዘርበት የሰነበተ መሆኑን ተከትሎ የከተማ አስተዳደሩ በንግድ ቢሮ በኩል ሊያሰራ የሚችል ዝርዝር የአፈፃፀም መመሪያ እስከ 2017 የበጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ ወጥቶለት ዓመቱ ከመጠናቀቁ በፊት ወደ ትግበራ ይገባልም ብሎ ነበር።

አሁን ያለንበት ወቅት የ2017 የበጀት ዓመት የተጠናቀቀበት እንደመሆኑ የተባለው ዝርዝር የአፈፃፀም መመሪያ ወጥቶ ወደ ትግበራ ተገባ ወይ? ስንል ስራውን እንዲመራ በከተማ አስተዳደሩ ሃላፊነት የተሰጠውን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ጠይቀናል።
አቶ አሸናፊ ብርሃኑ የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ናቸው።
እርሳቸው እንደሚሉት መመሪያው ለዝርዝር እይታ ፍትህ ሚኒስቴር እንደገባ ነው እስካሁን አልተመለሰልንም፤በዚህ ምክንያት በከተማዋ ምክር ቤት መጽደቅ ባይችልም አሁን ባለው ሁኔታ ወደ ትግበራ መግባት የግድ ነው፤ ከቅጣት ባሻገር ደምቡ ወደ ተግባር ገብቷል ብለውናል፡፡
የምሽት ስራ ያስፈለገው በከተማዋ በቀን ብቻ ሳይሆን በምሽትም ሊያሰራ የሚችል ኢኮኖሚ ለመፍጠር ነው።
ዝርዝር የአፈፃፀም መመሪያ የሚወጣው በየትኛው ስፍራ ያሉ፤ የትኞቹ የንግድ ዓይነቶች ላይ ህጉ ተፈፃሚ መሆን አለበት የሚለውን ለመለየት ነው፤ እስካሁን መመሪያው ስላልወጣ እነዚህን መለየት ባይቻልም በደፈናው በከተማ አስተዳደሩ በተዋቀረው ግብረ ሃይል ቁጥጥር እየተደረበት ነው ተብሏል።
ከሰሞኑ እንደሰማነው ማስተግበሪያ መመሪያው ሳይወጣ፤ የቢዝነስ ዓይቶቹም ተለይተው ሳይታወቁ የንግድ ቢሮ የስራ ሀላፊዎች ከደምብ ማስከበር ባለስልጣንና ከየክፍለ ከተማው የስራ ሀላፊዎች ጋር የምሽት የንግድ ስራዎች ትግበራ እየተዘዋወሩ እየቃኙ ነው።
ትግበራው እንዴት ሊጀመር ቻለ? ያልናቸው የንግድ ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ ብርሃኑ መስሪያ ቤታቸውን ጨምሮ ሌሎችም በተካተቱበት ግብረ ሃይል እየተተገበረ መሆኑን ነግረውናል።
የከተማ አስተዳድሩ በነጋዴው ማህበረሰብ የተፈጠረውን ስጋት ለማስወገድ ደጋግሞ በተለይ ፀጥታውን ለማስጠበቅ እሰራለሁ፤ በዚህ ስጋት አይግባችሁ፤ በተለይ አብዛኞቹ ነጋዴዎች አዲስ አበባ ሰርተው መዳረሻቸው ሸገር ከተማ እንደመሆኑ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በጉዳዩ ላይ እየሰራሁ ነው ብሎ ነበር።
በከተማዋ እየተከወኑ ስላሉ ስራዎች ለጋዜጠኞች ማብራሪያ የሰጡት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ወንድሙ ሴታ ከተማዋን ከዝግነት ክፍት ወደመሆን ያመጣት እንዲሁም እዚህም እዚያም ይፈፀም የነበረው የወንጀል ድርጊት እንዲቀንስ ያደረገው በየኮሪደሩ የተተከለው የመንገድ መብራት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከተማዋ አምሽቶ ለመስራት ምቹ ወደ መሆን እየመጣች መሆኑንም አቶ ወንድሙ አንስተዋል፡፡
እስከ ምሽት 3:30 ድረስ የንግድ ቤቶቹን መብራቶች አብርተውና ለተገልጋይ ክፍት አድርገው አገልግሎት የማይሰጡ ነጋዴዎች ከማስጠንቀቂያ በኋላ የ10 ሺህ ብር ቅጣት ይጠብቃቸዋል።
በሌላ በኩል የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች እስከ ምሽቱ 4:00 ሳያቆራርጡ በመጫን በተተመነው ታሪፍ ብቻ በማስከፈል አገልግሎት እንዲሰጡ ደምቡ ያስገድዳል።
ይህንን ሳያደርጉ ቢቀሩ ከማስጠንቀቂያ በኋላ የ5,000 ብር ቅጣት ይጠብቃቸዋል።
በግብረ ሃይሉ ከንግድ ስራው በተጨማሪ መሸት ሲል ጠብቀው እያቆራረጡ የሚጭኑና ከታሪፍ በላይ የሚያስከፍሉ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ስላሉ የሚደረገው ቅኝት ይህንንም ያጠቃልላል መባሉን ሰምተናል፡፡
ምንታምር ፀጋው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s











Comments