ሐምሌ 17 2017 -የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ ተግባራዊ ያደረገው የኦንላይን የተማሪዎች የፈተና አሰጣጥ ሥርዓት
- sheger1021fm
- Jul 24
- 1 min read
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ ያደረገው የኦንላይን #የተማሪዎች የፈተና አሰጣጥ ሥርዓት የሲስተም ችግር ገጥሞታል ፣ የተማሪዎችንም ውጤት ተመሳሳይ አድርጓል የሚሉና ሌሎች ቅሬታዎች ቀርበውበታል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በበኩሉ እስካሁን ባደረኩት ማጣራት ችግሩ ከሲስተሙ ጋር አለመናበብ እንጂ የሲስተሙ አይደለም ብሏል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ለርኒንግ አሰስመንት ሲስተም (learning assessment system) በሚል የሰራው የፈተና መስጫ ሥርዓት በተገቢው መንገድ ሙከራ አድርጌ ነው በዚህ አመት በስራ ላይ ያዋልኩት ብሏል፡፡
በቅርቡ በተሰጠው ፈተና የፈተና መስጫ ርዓቱ የሲስተም ችግር ገጥሞታል፣ የፈተና ሥርዓቱ በአንዳንድ የትምህርት መስኮች ላይ የተማሪዎች ውጤት ተመሳሳይ አድርጎ ነው ያወጣው የሚልና ሌሎችም ቅሬታዎች ደርሰውናል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፈተና ማዕከል ኃላፊ ብርሃኑ አበራ(ዶ/ር) የመጀመሪያ ዓመት የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ፈተና የወሰዱት አዲስ በለማው የለርኒግ አሰስመን የፈተና መስጫ ሥርዓት ነው ብለዋል፡፡
ዶክተር ብርሃኑን ይህ ቅሬታ በተመለከተ ምላሽ ሲሰጡ የተማሪዎች ውጤት ተመሳሳይ እንዲመጣ አድርጓል የሚለው ቅሬታ ከተማሪዎች ብቻ ሳይሆን ከመምህራንም ደርሶናል፡፡
ነገር ግን በመፈተኛ ሥርዓቱ ላይ በተደረገ ማጣራት የተባለው ጉዳይ አላገኘንም ብለዋል፡፡
አስፈላጊው ማጣራት አሁንም እያደረግን ነው በማለት ጠቅሰዋል፡፡
አንዳንድ መምህራን የተማሪዎች ውጤት ሲሰሩ ከ100 በመቶ በላይ ሰርተው አስገብተው ነበር ዩኒቨርሲቲው እየተጠቀመበት ያለው የውጤት ማሳወቂያ ሥርዓት ከ100 በመቶ በላይ የመጣ ውጤት አይቀበልም፡፡
በዚህ ምክንያት የአንዳንድ ተማሪ ውጤት ወደ ውጤት ማሳወቂያ ሥርዓቱ ሳይገባ ቀርቶ ነበር ብለዋል፡፡
ይህ ችግር መምህራን እንዲያስተካክሉ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ውጤት ተበላሽቶብናል የሚሉ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ክፍሉ አልያም ትምህርቱን ወዳስተማረው መምህር በመሄድ መነጋገርና ችግሩን መፍታት ይችላል ሲሉ ዶክተር ብርሃኑ ነግረውናል፡፡
በረከት አካሉ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
Comments