top of page

“ለኢትዮጵያ የቡና ምርታማነት የፋይናንስ አቅርቦት ዋነኛው ችግር ሆኗል” በሚል የአለም ባንክ ከሠሞኑ ይፋ ያደረገው ጥናት የተጋነነ እንደሆነ የኢትዮጵያ ቡና ፤ ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ተናገረ።

  • sheger1021fm
  • 5 minutes ago
  • 2 min read

ጥር 15/2018  

 

“ለኢትዮጵያ የቡና ምርታማነት የፋይናንስ አቅርቦት ዋነኛው ችግር ሆኗል” በሚል የአለም ባንክ ከሠሞኑ ይፋ ያደረገው ጥናት የተጋነነ እንደሆነ የኢትዮጵያ ቡና ፤ ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ተናገረ።

 

ከሚመለከተው ትክክለኛ ተቋም መረጃ ተወስዶ የተሰራ ጥናት ነው ብሎ እንደማያምንም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጠቅሷል።

 

ለኢትዮጵያ የቡና ምርታማነት የፋይናንስ አቅርቦት ዋነኛው ችግር እንደሆነ ከሠሞኑ ይፋ የሆነ የዓለም ባንክ ጥናት አሳይቷል።

 

የባንኩ ጥናት እንደሚለው በኢትዮጵያ የቡና ምርታማነት እንዳይሻሻል ፈተና ሆነው ከቀጠሉ ችግሮች መካከል የፋይናንስ አቅርቦት 90 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ይወስዳል።

 

ትራንስፖርት 51 በመቶ እና  አስተማማኝ ያልሆኑ የመሰረተ ልማት ተቋማት ችግር 13 በመቶ ድርሻ እንዳላቸውም ጠቅሷል።

 

የገበያ ተወዳዳሪነት ፤ እንዲሁም ከህጎች ጋር የተያያዙ ማነቆዎች የቡና ምርታማነት በኢትዮጵያ እንዳይሻሻል ያደረጉ ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው ብሏል።

 

በዚሁ የዓለም ባንክ ጥናት ላይ አስተያየቱን የጠየቅነው የኢትዮጵያ ቡና ፤ ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን የተጠቀሱት ችግሮች ተጋነው የቀረቡ ናቸው ብሏል።

 

በተለይ የፋይናንስ አቅርቦት ዋነኛው የዘርፉ ችግር ነው በሚል የቀረበው መረጃ የተጋነነ እንደሆነ የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የልማት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ታጋይ ኑሩ ነግረውናል።

 

የፋይናንስ አቅርቦት ችግር በዋናነት እየገጠማቸው ያሉት ቡና አምራች አርሶ አደሮች ናቸው የሚሉት አቶ ታጋይ እነሱም መፍትሄ እንዲያገኙ እየሰራን ነው ብለውናል።

 

ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመሆን ለአርሶ አደሮቹ ያለ ምንም ማስያዣ ባላቸው መሬት ልክ ብድር የሚሰጣቸው ባንክ እንዲቋቋም መደረጉን አመልክተዋል። 

 

በትራንስፖርት በኩል ያሉ ችግሮችንም ለመፍታት ቡናን በባቡር ማጓጓዝ እንደተጀመረ አቶ ተጋይ ተናግረዋል።

 

ወጣ ባሉና ቡና በሚመረትባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ካልሆነ በስተቀር አሁን ላይ የትራንስፖርት ችግር ብዙም የለም ነው ያሉት።

 

መሰረተ ልማቶችም ቢሆኑ ኢኮኖሚው በፈቀደ መጠን በሀገሪቱ እየተገነቡ ናቸው ያሉት ሃላፊው በተለይ ከፍተኛ የግብርና ምርቶች መገኛ የሆኑ አካባቢዎች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ስራው እየተከወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

 

ከገበያ ተወዳዳሪነት እና ከህጎች ጋር የተያያዙ ችግሮችንም ለመፍታት መንግስት እየሰራ እንደሚገኝ አቶ ታጋይ ተናግረዋል።

 

ቡና ከኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከ30 እስከ 35 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ እንደሚሸፍን ይነገራል።

 

ከ15 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ሰዎችም የስራ ዕድል ፈጥሯል ተብሏል ።

                            

ሙሉ ዘገባወን ያድምጡ…

 

ንጋቱ ረጋሣ

 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…..

 

X : https://x.com/shegerfm?s=2                 

Website፡ https://www.shegerfm.com/                          

 
 
 

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page