በአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያዎች ሊደርስ የሚችል የአደጋ ስጋት ሲኖር የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እርምጃ እንዲወስድ የሚፈቀድ ረቂቅ አዋጅ ወደ ቋሚ ኮሚቴ ተመራ፡፡
- sheger1021fm
- 3 hours ago
- 2 min read
ጥር 15/2018
በአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያዎች ሊደርስ የሚችል የአደጋ ስጋት ሲኖር የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እርምጃ እንዲወስድ የሚፈቀድ ረቂቅ አዋጅ ወደ ቋሚ ኮሚቴ ተመራ፡፡
በአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያዎች ላይ ከትከሻ የሚተኮስ የአየር መከላከያ መሳሪያ፣ ሰው አልባ አውሮፕላንን ጨምሮ ስጋት ማድረስ የሚችል ማንኛውም ሊቃጣ የሚችል የአደጋ ስጋት ሲኖር የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የመከላከል እርምጃ እንዲወስድ የሚፈቀድ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ነው ለቋሚ ኮሚቴው የተመራው።
ፓርላማው ወደ ቋሚ ኮሚቴ የመራው ረቂቅ የኢትዮጵያ የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ አዋጅ የመንገደኞችን ምዝገባ እና ቅድመ-በረራ መረጃ የመሰብሰብና የማሰራጨት ትግበራን እንዲመራ እና እንዲያስተባባር ለብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ሃላፊነት ይሰጣል።

የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ትናንት አካሂዶት በነበረው መደበኛ ጉባዔው የኢትዮጵያ የአቪዬሽን ሴኩዩሪቲ አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅን በሙሉ ድምጽ በዋናነት ለውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ፣በተባባሪነት ደግሞ ለከተማ መሰረት ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳይዎች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡
ማሻሻያ ረቂቁ በአውሮፕላን እና በማረፊያ ጣቢያዎች ላይ ሕገ-ወጥ ጣልቃ ገብነት ሊፈፀምባቸው የሚችሉ ከትከሻ የሚተኮስ የአየር መከላከያ መሳሪያ ወይም ስጋት ማድረስ የሚችል ማንኛውም ነገር አልያም ሰው አልባ አውሮፕላን ዝውውር ላይ ቁጥጥር ያደርጋል።
ሊቃጣ የሚችል አደጋን ለመከላከል የደህንነት እርምጃ ስርዓት ይዘረጋል፤እርምጃ ይወስዳል የሚል አዲስ አንቀጽ መካተቱንም ይዘረዝራል።
ምክንያቱን ሲያስረዳ ደግሞ በአየር ትራንስፖርት ላይ ጥቃት ሊፈፀምባቸው የሚችሉ ከሰው ትከሻ የሚተኮሱ የአየር መከላከያ መሳሪያዎች (MANPADS) ወይም ስጋት ማድረስ የሚችል ማንኛውም ነገር ወይንም ሰው አልባ አውሮፕላን (Drone) ዝውውርና እንቅስቃሴ ቁጥጥር ስለሚደረግበት እና በአውሮፕላን ጣቢያ አከባቢ ሊፈፀም የሚችልን ሕገ-ወጥ ድርጊትን ለመከላከል የሚያስችሉ የአቪዬሽን የደህንነት እርምጃ የሚወሰድበትን ስርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ እንደሆነ ረቂቁ ዘርዝሯል፡፡
የአየር ላይ በረራ ደህንነትን የበለጠ አስተማማኝ ለማድረግና የአባል አገራት ሉአላዊነት እንዲከበር ለማድረግ ይረዳል በሚል ምክንያትም የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ወደ ኢትዮጵያ የሚበሩ መንገዶች የበረራ ደህንነት ኦፊሰር ስምሪት ቁጥጥርና ክትትል እንደሚያደርግም ያዛል፡፡
አገልግሎቱ ብሔራዊ የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ጥራት ቁጥጥር የስራ ክፍል ያቋቁማል፤ ያለገደብ በማንኛውም ቦታ በመንቀሳቀስ የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ፖሊሲዎች፣ፕሮግራሞች እና መስፈርቶች አተገባበር ተገቢነት እንዲረጋግጥ፤ የእርምት እርምጃ እንዲወስድ እና እንዲያሶስድ መብት ይሰጣል፡፡
በተጨማሪም በአቭዬሽን ሴኪዩሪቲ አዋጅ ማሻሻያ ሪቂቁ ውስጥ እንዲካተት የተደረገው አዲስ አንቀጽ የመንገደኞችን ምዝገባ እና ቅድመ-በረራ መረጃ የመሰብሰብና የማሰራጨት ትግበራን ይመለከታል።
በዚህም መሰረት አገልግሎቱ ስራውን እንዲመራ እና እንዲያስተባብር የሚያዝ ነው፡፡
አገልግሎቱ የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም የመጠበቅ ሃላፊነት ያለበት በመሆኑ እና ከሌሎች አቻ ተቋማት ጋር በመተባበር አለም አቀፍ የወንጀል ሪከርድ ያላባቸው ተጠርጣሪዎችን የሚመለከት መረጃ በመለዋወጥ ክትትል በማድረግ ሽብርተኝነትና የተደራጁ ወንጀሎችን የመከላከል ሃላፊነትን ያለበት ተቋም መሆኑ እንደ ምክንያት ቀርቧል፡፡
በኤርፖርት የሚተላለፉ መንገደኞች መረጃ መቆጣጠር፣ተጠርጣሪዎችን መከታተል እንዲያስችለው የመንገደኞችን ምዝገባ እና ቅድመ-በረራ መረጃ የመሰብሰብና የማሰራጨት ትግበራን መምራትና ማስተባበር ያለበት መሆኑ ሌላው ምክንያት ነው፡፡
በኢትዮጵያ በኩል የሚጓዙ ተላላፊ መንገደኞች ከመነሻ ሀገር የሚደረግላቸው የደህንነት ፍተሻ አስተማማኝ መሆኑ ሲረጋገጥ መንገደኞች እና የጉዞ እቃዎቻቸው ከፍተሻ ነፃ ሊሆኑ የሚችሉበት ድንጋጌም ትናንት ለሁለቱ ቋሚ ኮሚቴዎች የተመራው አዋጅ ውስጥ አካቷል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…..
YouTube : https://url-shortener.me/2DTR
Telegram : https://t.me/ShegerFMRadio102_1
Facebook፡ https://url-shortener.me/2DTY
WhatsApp :https://url-shortener.me/2DU0
X : https://x.com/shegerfm?s=2
Website፡ https://www.shegerfm.com/
LinkedIn :https://url-shortener.me/2DU8
Tiktok : https://url-shortener.me/2DUB
Instagram : https://url-shortener.me/2DUD












Comments