top of page

በኢትዮጵያ የዲጂታል የክፍያ ሥርዓትን ለማዘመን ብሔራዊ ባንክ ከ20 ለሚበልጡ የዲጂታል ክፍያ አገልግሎት ሰጭዎች ፍቃድ መስጠቱ ይታወቃል።

  • sheger1021fm
  • 2 hours ago
  • 2 min read

ጥር 15/2018


በኢትዮጵያ የዲጂታል የክፍያ ሥርዓትን ለማዘመን እና በኢኮኖሚው ውስጥ የተቀላጠፈ የክፍያ ሥርዓት እንዲኖር ብሔራዊ ባንክ ከ20 ለሚበልጡ የዲጂታል ክፍያ አገልግሎት ሰጭዎች ፍቃድ መስጠቱ ይታወቃል።


በአጠቃላይ በዲጅታል የክፍያ አገልግሎት እንዲሰጡ ፈቃድ የያዙ የዲጂታል የክፍያ አገልግሎት አቀላጣፊዎች 26 ናቸው።


ከእነዚህ ከ26 ውስጥ ግማሽ ያህሎቹ በወደ ቢዝነስ ገብተው በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡


የተቀሩት 13 ግድም ደግሞ በሙከራ ደረጃ እየተፈተሹ እንደሆነ ሰምተናል።


ሰሞኑን ኢትዮጵያ ዲጅታል ኢኮኖሚ መንገድ ይከፍትልኛል ንግድ እና ቢዝነስ ያቀላጥፍልኛል ያለቻቸው ፤ የዲጅታል ሞባይል ባንኪንግ እና አጠቃላይ የክፍያ ሥርዓት የሚያስተላልፉ ፍቃድ ያገኙ አገልግሎት ሰጭዎች ፤ ታግደዋል ወይም በተወሰነ መንገድ እና በተለየ የአገልግሎት ዓይነት ብቻ አሉ የሚባል ወሬ ይሰማል።


ይህን በተመለከተ ለጉዳዮ ቅርብ የሆኑ ምንጫችን ጠይቀናል።


በቅድሚያ እነዚህ በዲጅታል ኢኮኖሚ ውስጥ ያሉት የክፍያ ሥርዓቶች ፤ ታግደዋል ወይ ስንል ጠይቀናል።


ከምንጫችን እንደተረዳነው ፤ እነዚህ ፍቃድ ከብሔራዊ ባንክ ያገኙ ዲጂታል ክፍያ ሥርዓት አቀላጣፊዎች አንዳቸውም እንዳልታገዱ ነው።


ስለዚህ እነዚህ አገልግሎት ሰጭዎች በስራ ላይ ናቸው።


ነገር ግን እነዚህ የዲጅታል ክፍያ ሥርዓት አቀላጣፊዎች በአሰራር ግድፈት ፤ በሀብት ማሸሽ ፤ በታክስ ስወራ እና በሌላም ለግዜው ማረጋገጥ ባልቻልነው ግድፈት በምርመራ ላይ መሆናቸውን አረጋግጠናል።

ፈቃድ የሰጣቸው ብሔራዊ ባንክ ሆኖ ሳለ የሚመረምራቸው ማነው የሚለውን ለማጣራት ሞክረናል።


ፈቃድ የሰጣቸው ማእከላዊ ባንኩ ሆኖ ሳለ ፤ እንደ ግድፈታቸው መጠን እና ስጋት በፋይናንስ ደህንነት ወይም በፍትህ ሚኒስቴር ወይም በፌደራል ፖሊስ ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሆነ አረጋግጠናል።


እነዚህ የዲጅታል የክፍያ ሥርዓት አቀላጣፊዎች ፤ ለምን ምርመራ ተከፈተባቸው ብለን ወደኋላም ምንጫችንን ጠይቀናል።


ለመረዳት እንደሞከርነው ኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብን ሰውረዋል የተባሉ ፤ በርካታ የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶች ባለቤቶች እና ተባባሪዎቻቸው ፤ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ፤ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መናገሩን ተከትሎ እንደሆነ አውቀናል።


ለመንግሥት ገቢ መሆን የነበረበትን ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ በመሰወር ወንጀል ተጠርጥረው ፤የተያዙት እንዳሉ በመጥቀስ እና በተወሰደው እርምጃ በደኅንነት አገለግሎቱ ፤በቁጥጥር ሥር የዋሉት የ24 የስፖርት አወራራጅ ድርጅት ባለቤቶች እና ተባባሪዎቻቸው መሆናቸው ተሰምቷል።


የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶቹ ፊንቴክ ወይም አግሪጌተር ተብለው ከሚጠሩ የፋይናንስ ሥርዓቶችን ከሚያካሂዱላቸው ፤ የአገር ውስጥ የክፍያ ሥርዓት አቅራቢ ተቋማት ጋር በመመሳጠር የገንዘብ ስወራውን ፈጽመዋል ተብሏል።


ፊንቴክ ወይም አግሪጌተር የሚባሉት የአገር ውስጥ የገንዘብ ክፍያ ሥርዓት አቅራቢ ፤ተቋማቱ ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ በመውሰድ የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡


ስለዚህ እነዚህ ድርጅቶች የደንበኛን ምሥጢር መጠበቅ የሚል ሙያዊ አሠራርን ፤ እንደ ሽፋን ተጠቅመው ፤ የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶች የሚያንቀሳቅሱትን ገንዘብ፤ከሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ደብቀዋል ወይንም አሳንሰው አቅርበዋል ተብሏል።


ይህን ተከትሎም የብሔራዊ መረጃ እና የደኅንነት አገልግሎት፤በዚህ የተነሳ የቤቲንግ የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶች በግብር ስወራ እንዲሁም ከፍተኛ የአገር ሀብትን ወደ ውጭ በማሸሽ ወንጀል ላይ ተሳትፎ እንዳላቸው ከዚህ ቀደም ተነግሮ ነበር።


የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የፀጥታ አካላት ግለሰቦቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል በጋራ መሥራታቸውም ተገልጿል።


ይህን ተከትሎም ፤ እነዚህ የዲጅታል የክፍያ ሥርዓት አቀላጣፊዎች ከፍተኛ ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሆነ ለጉዳዮ ቅርብ ከሆኑ ምንጫችን አረጋግጠናል።


እነዚህ ፈቃድ ከብሔራዊ ባንክ ያገኙ የዲጅታል ክፍያ ሥርዓት አቀላጣፊዎች፤ ህጉ ላይ በሰፈረው መሰረት እንዳጠፋት ዓይነት ጥፋት ፍቃድ እስከመነጠቅ እና ሌላም ብሔራዊ ቅጣት ሊያገኛቸው እንደሚችል አረጋግጠናል።


ተህቦ ንጉሴ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…..


X : https://x.com/shegerfm?s=2

Website፡ https://www.shegerfm.com/

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page