top of page

ለአበባ፤ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት በቂ መሬት እንዲቀርብ ከመንግስት ጋር ውይይት ተጀምሯል ተባለ

  • sheger1021fm
  • 22 minutes ago
  • 1 min read

ጥቅምት 25 2018


ለአበባ፤ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት በቂ መሬት እንዲቀርብ ከመንግስት ጋር ውይይት ተጀምሯል ተባለ።


በዘርፉ መሰማራት የሚፈልጉ ብዙ የሀገር ውስጥ እና የውጪ ባለሃብቶች እንዳሉም ተነግሯል።


የአበባ ፤ አትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ አሁን ላይ በዓመት በአማካይ ከ500 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ለኢትዮጵያ እንደሚያስገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ።


ከሁለት መቶ ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች የስራ ዕድል መፍጠሩንም የኢትዮጵያ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች እና ላኪዎች ማህበር ተናግሯል።


በ2.45 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ላይ እየተካሄደ ያለ ልማት መሆኑም ተጠቅሷል።


በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን እየተጠቀሙ መሆናቸውን የሚናገሩት የማህበሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ዘውዴ ፤ አለም አቀፍ ደረጃዎችን አሟልቶ ለመገኘትም ጥረት እያደረግን ነው ብለዋል።

ree

እንዲያም ሆኖ ግን የሚፈለገው ደረጃ ላይ ተደርሷል ማለት እንደማይቻል ተናግረዋል።


በተለይ ኢትዮጵያ ካላት እምቅ አቅም እና ከህዝቧ ቁጥር አንጻር ብዙ ይቀረናል ብለዋል።


የኢትዮጵያ የአበባ አትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ይበልጥ እንዲያድግ ማህበራቸው ከመንግስት ጋር በቅርበት እየሰራ እንደሚገኝ የነገሩን አቶ ቴዎድሮስ ፤ ልማቱን የተመለከተው ብሄራዊ ስትራቴጂ የተዘጋጀው እና ሌሎች ህጎች የወጡትም በዚሁ የጋራ ስራ እንደሆነ ጠቅሰዋል።


በዘርፉ ዙሪያ ከሚነሱ ጥያቄዎች አንዱ የመሬት አቀርቦት ጉዳይ ነው።


በስራው ላይ ያሉ ባለሃብቶች ተጨማሪ መሬት አግኝተው ልማቱን ለማስፋፋት ፤ ሌሎች ደግሞ እንደ አዲስ ፤ ወደ ስራው ገብተው ለማልማት የሚያቀርቡት የመሬት ጥያቄ በበቂ መጠን ምላሽ እያገኘ እንዳልሆነ ሲናገሩ ይሰማል።


በዚህም ጉዳይ ከመንግስት ጋር ውይይት እየተካሄደ እንደሚገኝ አቶ ቴዎድሮስ ተናግረዋል።


ባለንበት የ2018 በጀት ዓመት ወደ ውጪ ከሚላክ አበባ አትክልትና ፍራፍሬ 735 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት መታቀዱ ተነግሯል።


በ2017 በጀት አመት የተገኘው 564 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር እንደነበር የኢትዮጵያ አበባ ፤ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች እና ላኪዎች ማህበር አስታውሷል።

ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ…

ንጋቱ ረጋሣ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

👇👇👇


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page