top of page

ህዳር 2 2018 - የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር አለም አቀፍ ወድድሮችን በተመለከተ እቅዱን ሙሉ በሙሉ ፈጽሜያለሁ ማለቱ በፓርላማ ጥያቄ አስነሳ።

  • sheger1021fm
  • 5 hours ago
  • 2 min read

በ20ኛው አለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ ያመጣችው ውጤት ከ33 ዓመታት ወዲህ ዝቅተኛ ቢሆንም፤ የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር አለም አቀፍ ወድድሮችን በተመለከተ እቅዱን ሙሉ በሙሉ ፈጽሜያለሁ ማለቱ በፓርላማ ጥያቄ አስነሳ።


ኢትዮጵያ ባለፈው ጃፓን ቶኪዮ ላይ በተደረገው 20ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ያስመዘገበችው ውጤት ከ33 ዓመታት ወዲህ ዝቅተኛው መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተናግሯል።


ቋሚ ኮሚቴው ይህን የተናገረው የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴርን የ2018 ሩብ ዓመት የስራ ክንውን ሪፖርቱን ትናንት ከስዓት በኋላ በገመገመበት ወቅት ነው።


የቋሚ ኮሚቴውን ጥያቄ ያቀረቡት የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ተህቦ ምህረት ናቸው።


አቶ ተህቦ የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር በአህጉር እና አለም አቀፍ ውድድሮች ተሳትፎን በተመለከተ የ3 ወራት የስራ ክንውን ሪፖርቱን አፈጻጸማቸው መቶ በመቶ እና ከዚያ በላይ እንደሚል አስታውሰው ነገር ግን በጃፓን ቶክዮ በተካሄደው 20ኛው አለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሀገሪቱ ያስመዘገበችው ውጤት ዝቅተኛ ሆኖ እያለ መቶ በመቶ ስኬት ተብሎ ሪፖርት መደረጉ ከምን አንጻር ነው ሲሉ ጠይቀዋል ።

ree

ለውጤቱ መታጣት የነበሩ ዋና ዋና ምክንያቶችን ለመለየት እና ለማስተካከል የተሰሩ ስራዎች ምን እንደሆኑ የጠየቁት የምክር ቤት አባሉ የተወሰዱ ትምህርቶችን በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጥም ጠይቀዋል።


ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሚኒስትር ዴዔታ የሆኑት አቶ መክዩ ሞሀመድ ናቸው። አቶ መክዩ መቶ በመቶ ፈጽመናል ያልንው በተሳትፎ እንጂ ያመጣውን ውጤት አይደለም ብለዋል።


በየዓመቱ በየትኛውም ውጤት ማምጣት በምንችልባቸው ውድድሮች ላይ እንሳተፍ በሚለው ላይ እናቅዳለን ያሉት አቶ መክዩ ባለፉት ሶስት ወራት አሳካነው ያልነው ተሳትፎን ነው ሲሉ አስረድተዋል።


ለሁሉም ኢትዮጵያዊ አትሌቲክስ ከስፖርትም በላይ ነው የሚሉት ሚኒስቴር ዴዔታው ለዚህም ነው ሁሉም ውጤት የሚጠብቅበት የሆነው ብለዋል።


ሚኒስትር ዴዔታው በስፖርት ላይ ያለው ነገር አገር አቀፍ ስብራት ነው ያሉ ሲሆን በአገር አቀፍ ያሉን ፌዴሬሽኖች ተቋም ሆነው ስፖርቱን መምራት እና በእቅድ መምራት ላይ መሰረታዊ ችግር ነው ያለባቸው ሲሉ አስረድተዋል።


ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ይህን ችግር ለማስተካከል በቀጥታ የመሳተፍ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ለማሳያም በቶኪዮ የአለም ሻምፒዮና ዝግጅት ላይ በርካታ ስራዎችን ሰርተናል ብለዋል ሚኒስትር ዴዔታው።


የፌደሬሽኑ አመራሮች አዲስ ስለነበሩ እቅዶችን ከማቀድ ጀምሮ በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገቡ መስሪያ ቤቱ እገዛ ሲያደርግ ነበር ሲሉ አቶ መክዩ ተናግረዋል።


አንዱ የነበረው መሰረታዊ ችግር የትራክ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትር ዴዔታው አቶ መክዩ ሞሀመድ የአትሌቲክስ ውጤት መቀነስ የጀመረው ከፓሪስ ኦሎምፒክ ጀምሮ ነው ሲሉ አስረድተዋል።


በቶክዮ ሻምፒዮና የተገኘው ውጤት ካለን ታሪክ አንጻር ኢትዮጵያን የሚመጥን ስላልሆነ፤ ችግሩ ምንድነው የሚለውንም በሚኒስቴር መስሪያ ቤት ደረጃ ወይይት እንደተካሄደበት ተነግሯል።


አጠቃላይ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ዝርዝር ውይይት እንደተካሄደበት እና በዚህም የስልጠና ዝግጅት ማነስ፣ የቴክኖሎጂ ግብዓት ማነስ፣ የፌደሬሽኑ የማስፈፀም አቅም መዳከም እና በዚህም የሚመረጡ ሯጮች እና አሰልጣኞች አለመታዘዝ ለውጤቱ መጥፋት ዋነኛ ምክንያቶች ነበሩ ተብሏል።


ያሬድ እንዳሻው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

👇👇👇


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page