ህዳር 15 2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች
- sheger1021fm
- 3 minutes ago
- 2 min read
ከናይጄርያዋ ኒጀር ግዛት የአንድ የካቶሊክ ትምህርት ቤት ከታገቱት ከ300 በላይ ተማሪዎች መካከል ሃምሳው ከአጋቶቻቸው ማምለጣቸው ተሰምቷል፡፡
ጉዳዩን የሚከታተለው ቡድን 50ው ተማሪዎች ከአጋቾቻቸው ማምለጣቸውን አረጋግጫለሁ ማለቱን ቢቢሲ ፅፏል፡፡
ይሁንና በምን ሁኔታ እና ከየት እንዳመለጡ አላብራራም፡፡

አምላጮቹ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተቀላቅለዋል ማለቱ ተሰምቷል፡፡
የናይጀሪያ የፀጥታ ሀይሎች ታጋቾቹን ለማስለቀቅ በተቀናጀ አሰሳ ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡
ባለፈው ሳምንት መጀመሪያም በኬቢ ግዛት ከሚገኝ አንድ አዳሪ ትምህርት ቤት 20 ተማሪዎች ታግተው መወሰዳቸውን መረጃው አስታውሷል፡፡
እገታውን በመስጋት ብዙዎቹ የናይጀሪያ ግዛቶች ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ማድረጋቸው በመረጃው ተጠቅሷል፡፡
ሳውዲ አረቢያ በ1 ሳምንት ውስጥ ህገ-ወጥ ናቸው ያለቻውን ከ14 ሺህ በላይ የውጭ አገር ዜጎች ማባረሯ ተሰማ፡፡
የውጭ አገር ሰዎቹ የተባረሩት የአገሪቱን የድንበር ቁጥጥር እና የሰራተኝት ሕጎች ተላልፈው ተገኝተዋል ተብለው እንደሆነ ገልፍ ኒውስ ፅፏል፡፡
በጊዜውም ከ22,000 በላይ የውጭ አገራት ዜጎች በአሰሳ ተይዘው መታሰራቸው ታውቋል፡፡
እስር እና ከአገር ማባረሩ የተከናወነው በተለያዩ የፀጥታ አካላት ቅንጅት መሆኑ ታውቋል፡፡
ተባራሪዎቹ እና ታሳሪዎቹ በደፈናው የውጭ አገር ዜጎች ናቸው ቢባሉም በዘገባው ዜግነታቸው አልተጠቀሰም፡፡
ህገወጥ ናቸው የተባሉትን ዜጎች የመያዝ እና የማባረሩ ዘመቻ በመላ አገሪቱ መከናወኑን መረጃው አስታውሷል፡፡
በጊኒ ቢሳዎ ትናንት መጪውን ፕሬዘዳንት እና ቀጣዮቹን የፓርላማ አባላት ለመምረጥ የአገሪቱ ዜጎች ድምፅ ሲሰጡ ዋሉ፡፡
ለፕሬዘዳንታዊ ምጫው 11 እጩዎች መቅረባቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡
በምርጫው ቀጥታ አሸናፊ ለመሆን ከእጩዎቹ አንዱ ከ50 በመቶ በላይ ድምፅ ማግኘት ይጠበቅበታል ተብሏል፡፡
ፕሬዘዳንት ኡማሮ ኢምባሎ ሲስኮ የተፎካከሩት ለ2ኛ ጊዜ መሪነታቸው ለማፅናት መሆኑ ታውቋል፡፡
የጊኒ ቢሳዎ ምርጫ የተካሄደው ዋነኛው ተቃዋሚ የፖለቲካ ማህበር ባልተካፈለበት አጋጣሚ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
ዋነኛው ተቃዋሚ የፖለቲካ ማህበር ከምርጫው ውጭ የተደረገው በጊዜው የተሳትፎ ማመልከቻ ባለማቅረቡ ነው መባሉ ተሰምቷል፡፡
ጊኒ ቢሳዎ ፖለቲካዊ መረጋጋት የራቃት አገር እንደሆነች መረጃው አስታውሷል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬይኑን ጦርነት ለማስቆም አቅርበውታል በተባለ እቅድ ላይ ከዩክሬይን እና ከአውሮፓውያን ደጋፊዎቿ ጋር የሚካሄደው ንግግር ታላቅ እርምጃ እየታየበት መሆኑን የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናገሩ፡፡
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በጄኔቫ ስዊዘርላንድ የሚካሄደው ንግግር መልካም ውጤቶች እየታዩበት ነው ስለማለታቸው ቢቢሲ ፅፏል፡፡
ሩቢዮ ንግግሩ ቀሪ ጉዳዮችም እንዳሉት አልሸሸጉም፡፡
የዩክሬይኑ ፕሬዘዳንት ቮሎሚር ዜሌንስኪ የፕሬዘዳንት ትራምፕ የተደራዳሪዎች ቡድን የእኛንም ወገን ሀሳብ የመስማት ምልክቶችን እያሳየ ነው ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
በእቅዱ ላይ ምን ለውጥ እና ማሻሻያ እንደተደረገበት ግን የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡
የዚህን ንግግር ውጤት የተመለከተ ሰነድ ለሩሲያ እንደሚቀርብም ታውቋል፡፡
ቀደም ሲል የሩሲያው ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን እቅዱ ለዘላቂ ሰላም ለሚካሄደው ድርድር መሰረት የሚጥል ነው ማለታቸውን መረጃው አስታውሷል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
👇👇👇
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s








