ጋዛ ውስጥ የቆዩ የውጭ ሀገራት ዜጎች በራፋ ኬላ በኩል ወደ ግብፅ መጓዛቸው ተሰማ፡፡
በመቶዎች የሚቆጠሩ የውጭ ሀገራት ዜጎች በራፋ መተላለፊያ በኩል ወደ ግብፅ እንደገቡ ሲቢኤስ (CBS) ፅፏል፡፡
የራፋ መተላለፊያ ኬላ ከጋዛ ለሚመጡ ሰዎች ክፍት ሲደረግ ከወር ገደማ በኋላ የትናንቱ የመጀመሪያው ነው ተብሏል፡፡
እስራኤል ከሐማስ ጋር በምታካሂደው ጦርነት ጋዛን ክፉኛ እየደበደበችው ነው፡፡
በድብደባው ሰላማዊ ሰዎች ሳይቀሩ እየተገደሉ መሆኑ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
የውጭ ሀገር ዜጎች እና የውጭ ፓስፖርት የያዙ ሰዎች በራፋ በኩል ወደ ግብፅ እንዲያልፉ ካታር ዋነኛው አደራዳሪ ነበረች መባሉ ተሰምቷል፡፡
ከውጭ ዜጎቹ በተጨማሪ በእስራኤል ድብደባ ብርቱ አካላዊ ጉዳት የገጠማቸውም በራፋ በኩል ወደ ግብፅ መሻገራቸው ታውቋል፡፡
የእስራኤል ጦር የሐማስን የመከላከያ መስመር ሰበርኩት አለ፡፡
እግረኛው ሀይል በአየር እና በባህር ድብደባ እየተረዳ ወደፊት መግፋቱን አዛዦቹ እንደተናገሩ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
ጦሩ ወደ ጋዛ ከተማም በእጅጉ ተጠግቻለሁ ማለቱ ተሰምቷል፡፡
በጋዛ ጦርነቱ በተፋፋመበት አጋጣሚ የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን ጦርነቱ ጋብ እንዲል መጠየቅ እንደጀመሩ ተሰምቷል፡፡
ባይደን ጦርነቱ ጋብ እንዲል የጠየቁት ሐማስ ያገታቸውን ሰዎች ለማስለቀቅ ታልሞ ነው ተብሏል፡፡
ሐማስ ከ3 ሳምንታት በፊት እስራኤል ውስጥ በፈፀመው ድንገት ደራሽ ጥቃት አግቶ ወደ ጋዛ የወሰዳቸው ከ200 በላይ ታጋቾች እጁ እንዳሉ ይነገራል፡፡
ቀደም ሲል በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲደረግ የቀረቡ የተኩስ አቁም የውሳኔ ሐሳቦች ተቀባይነት ያላገኙት አሜሪካ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብቷን ተጠቅማ ውድቅ ስላደረቻቸው ነው፡፡
የሩሲያው የመከላከያ ሚኒስትር ሰርጌይ ሾይጉ ለዩክሬይን ከምእራባዊያን ቃል የተገቡላትን F-16 የጦር ጄቶችን በሙሉ ደጋ አመድ ማድረጋችን አይቀርም አሉ፡፡
ሾይጉ ለዩክሬይን የሚሰጧትን F-16 የጦር ጄቶች ለማውደም ከ20 ቀናት በላይ አይፈጅብንም ማለታቸውን አናዶሉ ፅፏል፡፡
የሩሲያው የመከላከያ ሚኒስትር ባለፈው ወር የአገራቸው የአየር መከላከያ ምድብተኞች የዩክሬይንን 37 የጦር ጄቶች እንደጣሉ ተናግረዋል፡፡
ይህም ብዛት አሁን ለዩክሬይን ከሚሰጧ F-16 የጦር አውሮፕላኖች የበለጠ እንደሆነ ሾይጉ አስታውሰዋል፡፡
ዩክሬይን አሜሪካ ስሪቶቹ F-16 የጦር አውሮፕላኖች ለዩክሬይን የተፈቀዱላት ከብዙ ደጅ ጥናት በኋላ እንደሆነ ዘገባው አስታውሷል፡፡
የታይዋን የመከላከያ ሹሞች የቻይና የጦር አውሮፕላኖች እና መረከቦች በአካባቢያችን እያዣበቡ ነው አሉ፡፡
እስከ ትናንት በነበሩት 24 ሰዓታት 43 የቻይና የጦር አውሮፕላኖች እና 7 የጦር መርከቦች በታይዋን አቅራቢያ ታይተዋል ማለታቸውን አናዶሉ ፅፏል፡፡
ቻይና ከሰደደቻቸው የጦር አውሮፕላኖች 37ቱ የታይዋንን የአየር ክልል መጣሳቸውን ተናግረዋል፡፡
ታይዋን ራሴን የቻልኩ አገር ነኝ ብትልም ቻይና ታይዋንን እንዳፈነገጠች ግዛቷ አድርጋ ትቆጥራታለች፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜም የታይዋንን የዲፕሎማሲያዊ እውቅና አድማስ እያጠበበችባት መሆኑ ይነገራል፡፡
ቻይና በታይዋን ጉዳይ ስሜተ ስሱ እንደሆነች ዘገባው አስታውሷል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz
Comments