‘’ኢትዮጵያ ውስጥ ድርቅ ቢከሰትም የአንድም ሰው ህይወት አላለፈም’’ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ውስጥ በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በሌሎች አካባቢዎች ድርቅ መከሰቱን ጠቅሰዋል፡፡
‘’አሁን ተከስቷል የተባለው ድርቅ ወደ ረሃብ ተቀይሮ የሰዎችን ህይወት እየቀጠፈ ነው የተባለው ፍፁም ውሸት ነው’’ ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማ አባላቱ እንደተናገሩት ‘’በተያዘው የምርት ዘመን ከፍተኛ የሆነ ምርት እንደ ሀገር ተመርቷል፣ ርሃብ እንደ ሀገር ቢከሰት ከዚህ ምርት በመጠቀም መቋቋም እንችላለን’’ ብለዋል፡፡
‘’ከዚህ ባለፈ የሚነሳው ነገር ፖለቲካዊ ይዘትን ያዘለ እንጂ ከእውነት የራቀ ነው’’ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እንደ ሀገር አስከፊ ረሃብ ከተከሰተ መንግስት ያሉትን አቅም በመጠቀም ችግሩን ለመፍታት እንደሚሰራም ጠቅላይ ሚንስትሩ ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አባልት አስረድተዋል፡፡
‘’ድርቁን ለመከላከል በሚደረገው ስራ ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው መንግስት ነው’’ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘’መንግስት ድርቁን ለመከላከል ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ በማውጣት ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እንዲሆን አድርጓል’’ ብለዋል፡፡
‘’ወደፊትም ፕሮጀክቶችን በማጠፈም ጭምር ድርቁ በዜጎች ህይወት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ እንሰራለን’’ ብለዋል፡፡
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments