top of page

የካቲት 26፣2016 - የባህር ማዶ ወሬዎች

 

የሔይቲ የተደራጁ የወሮበላ ቡድኖች መሪዎች የጠቅላይ ሚኒስትር ኤሪያል ሔነሪ መንግስት ሥልጣን እንዲለቅ ማስገደጃ ማቅረባቸው ተሰማ፡፡

 

የተደራጁት የወሮበላ ቡድኖች መሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ካቢኔያቸው ስልጣን መልቀቅ አለባቸው ያሉት ታላቅ የእስር ቤት ሰበራ ከፈፀሙ በኋላ እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡

 

በእስር ቤት ሰብረው በጥቂቱ 3 ሺህ 700 እስረኞች ማምለጣቸው ተነግሯል፡፡

 

በእስር ቤት ሰበራው ካመለጡት መካከል በቀድሞው ፕሬዘዳንት ግድያ ታስረው የቆዩም ይገኙበታል ተብሏል፡፡

 

በሔይቲ የፀጥታ መደፍረሱ እና ሥርዓተ አልበኝነቱ እየተባባሰ መምጣቱ ተጠቅሷል፡፡

 

የወሮበላ ቡድኖቹ የኤሪያል ሔነሪ መንግስት ስልጣን ካልለቀቀ የተደራጀ ጥቃታቸውን እንደሚያፋፍሙ መዛታቸው ተሰምቷል፡፡

 


 

የቀድሞ የአሜሪካ የአየር ሀይል የጥበቃ ባልደረባ ጥብቅ ወታደራዊ ሚስጥራዊ ሰነዶችን በየድረ ገፁ በማስወጣቱ በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ተባለ፡፡

 

ጃክ ቴክሴሪያ የተባለው የ22 አመት የቀድሞ የአሜሪካ አየር ሀይል የጥበቃ ባልደረባ በስራው አጋጣሚ እጁ የገቡትን ወታደራዊ ካርታዎች እና የሳታላይት ምስሎችን በድረ ገፅ እዩልኝ ሲል መቆየቱን ቢቢሲ ፅፏል፡፡

 

የግለሰቡ ድርጊት የአሜሪካ የጦር አጋሮችንም ሚስጥር አደባባይ ያሰጣ ነው ተብሏል፡፡

 

አቃቢያነ ህግ ጃክ ቴክሴሪያ ከ16 አመታት በላይ እስር እንዲፈረድበት መጠየቃቸው ተሰምቷል፡፡

 

ከ50 ሺህ ዶላር ያላነሰም የገንዘብ መቀጮ ይቆነደዳል ተብሏል፡፡

 

የግለሰቡ ድርጊት የአሜሪካ የመከላከያ መስሪያ ቤት (ፔንታገን) የጥብቅ መረጃ አያያዙን ዳግም እንዲፈትሽ ጭምር ያስገደደ መሆኑን ዘገባው አስታውሷል፡፡

 

 

ሩሲያ ጀርመን ሩሲያ ውስጥ ጥቃት ለመፈፀም እያሴረች ስለመሆኑ ተጨባጭ ማስረጃ አግኝቻለሁ አለች፡፡

 

የሩሲያ ሹሞች የጀርመን የጦር አለቆች ስለዚሁ ጉዳይ መመካከራቸውን የሚያስረዳ የድምፅ ቅጂ ቅጂ አግኝተናል ማለታቸውን ዴይሊ ቢስት ፅፏል፡፡

 

የድምፁ ቅጂውንም ስሙልን ብለው እንደለቀቁት ተሰምቷል፡፡

 

የክሬምሊኑ ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ የድምፅ ቅጂው የጀርመንን ጦር ፍላጎት በግላጭ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

 

ቀደም ሲል የፈረንሳዩ ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ ወታደሮቹን ወደ ዩክሬይን እንደሚልክ ፍንጭ ሰጥተው ነበር፡፡

 

ሆኖም ጀርመንና ሌሎች የኔቶ አባላት እኛ ወታደሮቻችንን በጭራሽ ወደ ዩክሬይን አንልክም ያሉት ወዲያውኑ ነበር፡፡

 

ሩሲያ ኔቶ ወታደሮቹን ወደ ዩክሬይን ከላከ ወደ ቀጥተኛ እና ታላቅ ግጭት ይከተናል ስትል አስጠንቅቃለች፡፡

 

 

የአሜሪካ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዶናልድ ትራምፕ ሪፖብሊካዊውን የፖለቲካ ማህበር ወክለው በፕሬዘዳንታዊ እጩነት ለመቅረብ በፉክክሩ መቀጠል ይችላሉ አለ፡፡

 

የኮሎራዶ ፣ ግዛት ቀደም ሲል ትራምፕ በሪፖብሊካዊው የፖለቲካ ማህበር እጩነት መቅረብ አይችሉም ብሎ እንደነበር ቢቢሲ አስታውሷል፡፡

 

በኮሎራዶ ግዛት ትራምፕ ከምርጫ ፉክክሩ ውጭ ሊሆኑ ይገባል የተባለው ከ4 አመታት በፊት ደጋፊዎቻቸው የአሜሪካ ፌዴራላዊ እንደራሴዎች መምከሪያ የሆነውን ካፒቶል ሂልን በደጋፊዎቻቸውን አስወርረዋል በሚል ምክንያት ነው፡፡

 

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ግን በፌዴራል ምርጫ ጉዳይ ግዛቶች አያገባቸውም የሚል ትዕዛዝ መስጠቱ ተሰምቷል፡፡

 

የቀድሞው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይሄን ቢወጡትም ሌሎች ክሶች እንደሚጠብቋቸው በዘገባው ተጠቅሷል፡፡

 

 

የኔነህ ከበደ

 

 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

 

 

 

Komentarze


bottom of page