አንዳንድ የግል ድርጅቶች የሠራተኞቻቸውን ትክክለኛው የጡረታ መዋጮ እንዳይሰበሰብ ደመወዝ አሳንሰው ያሳውቃሉ ተባለ።
- 4 days ago
- 2 min read
ግንቦት 11/2018
አንዳንድ የግል ድርጅቶች የሠራተኞቻቸውን ትክክለኛው የጡረታ መዋጮ እንዳይሰበሰብ ደመወዝ አሳንሰው ያሳውቃሉ ተባለ።
ድርጅቶቹ እስከ ሶስት ወር ሳይከፍሉ ከቆዩ ከሒሳብ ደብተራቸው ላይ እቀንሳለሁ ብሏል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራትም ከ39 ቢልዮን ብር በላይ ከግል ድርጅት ሰራተኞች ተሰብስቧል ያለው ተቋሙ ከስምንት ዓመት በፊት ከነበረው ገቢው የ34 ቢልዮን ብር ብልጫ አለው ብሏል፡፡
አንድ እና ከአንድ በላይ ሠው የቀጠረ ማንኛውም የግል ድርጅት ሠራተኛውን ወደ ጡረታ አቅድ የማስገባት ግዴታ እንዳለበት የግል ድርጅት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር አስታውሷል፡፡
የጡረታ መዋጮ ከሠራተኛውም ፤ ከቀጣሪውም ድርጅት ተቀንሶ በጊዜው ገቢ መሆን እንዳለበት ነው የአስተዳደሩ የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ስራ አስፈጻሚ አቶ መሠረት ዘለቀ የተናገሩት።
ከሠራተኛው ሰባት በመቶ፣ ከአሠሪው ደግሞ 11 በመቶ ተቆርጦ በአጠቃላይ 18 በመቶ በየወሩ ለአስተዳደሩ ገቢ መሆን እንዳለበት ነው ይህንኑ አስመልክቶ በወጣው ህግ ላይ የተደነገገው፡፡
ከሠራተኞች ላይ ተቀናሽ ተደርጎ ነገር ግን ገቢ ካልሆነ ራሱ ድርጅቱ ይከፍላልም ይላሉ ህጉ።
መዋጮውን በጊዜው ገቢ ማድረግ ላይ ግን በብዙዎቹ የግል ድርጅቶች ዘንድ አሁንም ሰፋ ያለ ችግር ይታያል ብለዋል።
አንዳንዶቹ የሠራተኞቻቸውን ደመወዝ አሳንሶ በማሳወቅ ትክክለኛ የጡረታ መዋጮ እንዳይሰበሰብ እንደሚያደርጉ ነው የጠቀሱት።
እንደ መፍትሄም ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል በአገር አቀፍ ደረጃ እስኪወጣ ድረስ ድርጅቶቹ ታክስ የከፈሉበትን የደመወዝ መጠን በማየት ፤ የጡረታ መዋጮው በዚያ ልክ እንዲከፈል ለማድረግ መታሰቡን ነግረውናል።
ሙሉ ለመሉ መዋጮ በማይከፍሉ ድርጅቶች ላይም ጠበቅ ያለ ክትትል በማድረግ ወደ ስርአቱ ለማስገባት እንሰራለን ብለዋል።
የሠራተኞቻቸውንም ፤ የድርጅታቸውንም የጡረታ መዋጮ ቀንሰው በጊዜው ገቢ የማያደርጉ ተቋማት ግን ፤ ራሳቸውን ላልተገባ ቅጣት እና ወለድ እየዳረጉ መሆናቸውን ማወቅ አለባቸው ሲሉ አቶ መሠረት ተናግረዋል፡፡
መዋጮውን በጊዜው ገቢ የማያደርጉ ድርጅቶች ከተደረሰባቸው የራሳቸውን እና የሰራተኛውን ክፍያ ከወለድ እና ቅጣት እንዲከፍሉ ይደረጋል ተብሏል።
የጡረታ መዋጮውን በጊዜው ገቢ የማያደርጉ ድርጅቶች ሃብት ንብረታቸው እንዲሸጥ ጭምር ሊደረግ እንደሚችል ተጠቅሷል።
አስተዳደሩ በ2018 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት 39.7 ቢሊየን ብር የጡረታ መዋጮ መሰብሰቡንም ሠምተናል።
ከስምንት ዓመት በፊት በዓመት ይሰበሰብ የነበረው የጡረታ መዋጮ አምስት ቢሊየን ብር እንደሆነ ስራ አስፈጻሚው አስታውሰዋል።
አስተዳደሩ በ2018 ሙሉ ዓመት 55 ቢሊየን ብር የጡረታ መዋጮ ለመሰብሰብ አቅጃለሁ ነው ያለው።
አሁን ላይ በግል ድርጅቶች የሚሰሩ 2.5 ሚሊየን ሰዎች በጡረታ አቅድ መሸፈናቸው ተጠቅሷል።
የግል ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች ከደመወዛቸው ላይ የተቆረጠ የጡረታ መዋጮ በትክክል ገቢ ስለመሆን አለመሆኑ
እንዴት ማረጋገጥ ይችላሉ?
ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ….
ንጋቱ ረጋሣ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
YouTube : https://shorturl.at/18TS1
Telegram : https://shorturl.at/68aeK
Facebook፡ https://shorturl.at/tm5Q4
WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx
LinkedIn: https://shorturl.at/Vfe6i
Tiktok : https://shorturl.at/lhYiv
Instagram: https://shorturl.at/9X4S7





Comments