በስዊድን ኤም ፖክስ(Mpox) በተሰኘው የዝንጀሮዎች ፈንጣጣ የተያዘ አዳጊ መገኘቱ ተሰማ፡፡
ለአገሪቱም የመጀመሪያው እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
በስዊድን የተገኘው በ M ፖክስ የተያዘ አዳጊ በቅርቡ ከአፍሪካ የተመለሰ ነው ተብሏል፡፡
በሽታው ባለፉት 8 ወራት በኮንጎ ኪንሻሣ 450 ሰዎችን እንደገደለ መረጃው አስታውሷል፡፡
የበሽታው ልውጥ ዝርያ በአፍሪካ ማዕከላዊ እና ምስራቃዊ ክፍል በመዛመት ላይ ነው ተብሏል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት በሽታው አለም አቀፍ የጤና ስጋት እንደሆነ አውጇል፡፡
የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከያ እና መቆጣጠሪያ አካል (CDC) አፍሪካም ቀደም ብሎ ኤም ፖክስ አህጉራዊ የጤና ስጋት ነው እንዳለው መረጃው አስታውሷል፡፡

በሱዳን አዲስ የኮሌራ ወረርሽኝ መቀስቀሱ ተሰማ፡፡
ወረርሽኙ ከተቀሰቀሰ ሳምንት ማስቆጠሩን ሱዳን ትሪቢዩን ፅፏል፡፡
300 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው ተረጋግጧል፡፡
በበሽታው የ18 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ታውቋል፡፡
የከሰላ አካባቢ ወረርሽኙ የበረታበት ነው ተብሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት የሚጥለው ዶፍ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ የወረርሽኙን መስፋፋት ማግባሱ ተሰምቷል፡፡
ከኮሌራ በተጨማሪ እንደ ወባ ያሉ በሽታዎች በወረርሽኝ ደረጃ እየተስፋፉ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በሱዳን ጦርነት መካሄድ ከጀመረ አመት ከ4 ወራት ማስቆጠሩ ይታወቃል፡፡
የቬኔዙዌላ ፖለቲካዊ ቀውስ እየተባባሰ ነው ተባለ፡፡
በቅርቡ የተካሄደው ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ውጤት ማወዛገቡን እንደቀጠለ አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡
የአገሪቱ የምርጫ አከናዋኝ መስሪያ ቤት በምርጫው ያሸነፉት በሀላፊነት ላይ የሚገኙት ግራ ክንፈኛው ኒኮላስ ማዱሮ እንደሆኑ ካወጀላቸው ሰንብቷል፡፡
ተቃዋሚዎቹ በፊናቸው በምርጫው ያሸነፉት እኛ ያቀረብናቸው እጩ ናቸው እያሉ ነው፡፡
የብራዚሉ ፕሬዘዳንት ሉላ አናሲዮ ዴ ሲልቫ ለውዝግቡ መፍትሄ ምርጫው ይደገም ቢሉም የተቃዋሚ መሪዋ በጭራሽ አንቀበልም ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
ኮሎምቢያም መሰል የመፍትሄ ሐሳብ ማቅረቧ ታውቋል፡፡
የቬኒዙዌላው ቀውስ ለገላጋይም አስቸግሮ እንደሚገኝ በመረጃው ተጠቅሷል፡፡
የኔነህ ከበደ
Comentários