ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ(ህወሐት) ህጋዊ ሰውነቴ ይመለስልኝ ሲል ጥያቄ አቀረበ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህጋዊ ሰውነቱን እንዲመልስለት በደብዳቤ ጠይቋል፡፡
የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ ሽብርተኛ ተብሎ ተፈርጆ የነበረው ሕውሀት በምርጫ ቦርድም ህጋዊ ሰውነቱ ተሰርዞ እንደነበር በደብዳቤው አስታውሷል፡፡
ይሁንና ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ከአሸባሪነት ዝርዝር መፋቁን በማስታወስ ከፌዴራል መንግስትም ጋር በመግባባት እየሰራሁ ነው ያለው ሕወሃት ቦርዱ የድርጀቱን ህጋዊ ሰውነት ወደ ነበረበት እንዲመልስ የሚጠይቅ ደብዳቤ አስገብቷል፡፡

ደብዳቤው ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት እና ለጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤትም በግልባጭ እንዳስገባ ከሰሞኑ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፃፈው ደብዳቤ ያመለክታል፡፡
ሕወሃት ህጋዊ ሰውነቱን መልሶ ካላገኘ ዋጋ እንደሌለው እና ህጋዊ ሳይሆን የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ወደ ዳግም ጦርነት ሊያስገቡ እንደሚችሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በነበራቸው ውይይት መናገራቸው ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ የምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ - ምግባር አዋጅም ሕወሃት ዳግም ህጋዊ እውቅና እንዲያገኝ የሚያስችለው ሆኖ መሻሻሉ እና በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት መፅደቁም አይዘነጋም፡፡
ትዕግስት ዘሪሁን
Comments